መሪና ተባባሪ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ የመሪና የተባባሪ ድርሻን ከሚገልጡ ታሪኮች አንዱ የሙሴና፣ የአሮንና የሖር ታሪክ ነው(ዘጸ. 17÷8-16)፡፡

    አማሌቃውያን ከእስራኤል ጋር ሲዋጉ ኢያሱ ጎልማሶቹን ይዞ ከአማሌቃውያን ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ሙሴ ደግሞ ወደ ኮረብታው ወጣ፡፡ ሙዜ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርጋሉ፡፡ ሙሴ ደክሞት እጁን ባወረደ ጊዜ ደግሞ አማሌቅ ድል ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሙሴ ቀኑን ሙሉ ዋለ፡፡ በመጨረሻ ግን የሙሴ እጆች ከበዱ(ደከሙ)፡፡ ይህን የተመለከቱት አሮንና ሖር ለሙሴ የድንጋይ ወንበር አዘጋጁለት፤ ሙሴም እዚያ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እጁን ዘረጋ፡፡ ድሉም ለእስራኤል ሆነ፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙሴ እጆቹ እየደከሙ መጡ፡፡ አሮንና ሖርም በግራና በቀኝ ሆነው የሙሴን እጆች ከፍ አድርገው ደገፏቸው፡፡ ያን ጊዜ ሙሴ እጆቹን አነሣ፡፡ እስራኤልም አማሌቅን ፈጽመው ድል አደረጉ፡፡

    አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆው ብቻውን አይደለም፡፡ እንኳንና በሰዎች የተመረጠ መሪ እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ እንኳን ብቻውን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ መሪ ምን ጠቢብ፣ ጎበዝ፣ ውጤታማ፣ ተወዳጅና ዐቅም ያለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሙሴ እጆች መዛሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ አሮንና እንደ ሖር መንገዱን አይቶ የሚደግፈው ይፈልጋል፡፡ መልካም መሪ ውሳኔዎቹ፣ የለውጥ ሐሳቦቹ፣ ዕቅዶቹና ቃል ኪዳኖቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያበረቱት እንደ አሮንና ሖር የመሳሰሉ አጋዦች ያስፈልጉታል፡፡ አሮንና ሖር ለሙሴ የተሰጠው ሃላፊነት ወይም ራዕይ አልተሰጣቸውም፡፡ ነገር ግን ሙሴን ደግፈው የሚፈልጉትን ውጤት አመጡ፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ባይሆንም የመልካም መሪን ሐሳብ፣ ዕቅድ፣ ራእይና ውሳኔ በመደገፍ ግን ለውጥ ማምጣት ይችላል፡፡

    ሙሴ አንድ ሲሆን ደጋፊዎቹ ግን ሁለት ነበሩ፡፡ ምንጊዜም ከደጋፊዎች ተደጋፊዎች ያንሳሉ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለምን የለወጧት ጥቂት ባለ ተሰጥዖዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸውን፣ መንገዳቸውን፣ አመራራቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ጥረታቸውን የሚደግፉ አካላቶች ነበሯቸው፡፡  በቤተክርስቲያንም መርሁ አንድ ነው የቤተክርስቲያን መሪዎች እንዲሁም የየአገልግሎት ክፍል መሪዎች ሊደገፉ አይዞአችሁ ሊባሉ ከጎናችሁ ነን ሊባሉ ይገባቸዋል፡፡ መሪዎች ወይም ቤተክርስቲያንን ወደታየላት ግብ ለማድረስ ራዕይ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ባለራዕዮች ስኬታማ የሚሆኑት የአገልግሎት ክፍሎች፣ በተለያየ ጸጋ የሚያገለግሉ አገልጋዮች፣ እንዲሁም ምዕመናን፣ ማግኘታቸው መሆኑን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡

     ብዙ ሙሴዎች እንደ አሮንና ሖርን የመሰሉ አጋዦች አጥተው እጃቸው ዝሎ ድል ሆነዋል፡፡ መንገዱ፣ ሐሳቡ፣ ውጣ ውረዱ፣ ሙግቱ፣ ጭቅጭቁ፣ የሰው ትችትና ወቀሳ፣ ስድብና ዕንቅፋትነት አዝሏቸው ድል ከማድረግ ድል ወደመሆን ወርደዋል፡፡ በህይወት ዘመናችን ብዙ ሙሴዎች ተሰጥተውን ነበር፡፡ነገር ግን የሚያግዛቸውና ክንዶቻቸውን የሚደግፍ፤ ቢያንስ የድንጋይ መቀመጫ እንኳ የሚሰጥ አጥተው በሞትና በሽፈት ድል እየሆኑ ተገቢውን ለውጥ ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡ ኧረ እንደውም ድንጋዩን እንዲቀመጡበት ከማድረግ ይልቅ ድንጋዩን እየወረወርን የፈነከትናቸው ስንቶች ይሆኑ ?

      ድል የማድረጊያ አንዱ መንገድ ብርቱዎቹን መደገፍ ነው፤ ክንዳቸው፣ ድምጻቸው፣ ሥራቸው፣ ጥረታቸው፣ ሐሳባቸው፣ ራዕያቸው ከፍ ሲል ድል እንዲያደርጉ መደገፍ ነው፡፡ መጥፎ ሠሪዎችን የምንቃወመውን ያህል መልካም ሠሪዎችን የማንደግፍ ከሆነ ውጤት አናመጣም፡፡

የሙሴም ታላቅነት ምን መሪ ቢሆን፣ እጆቹ ታላቅ ሥራ የሚሠሩና ድል አድራጊ ቢሆንም ሊደክም፣ ሊሸነፍ፣ ሊያቅተውና ሊዝል እንደሚችል አመነ፡፡ ያለ ሌሎች ድጋፍ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ተቀበለ፡፡ ታላቅነት ማለት የታናናሾችን አስተዋጽዖ መናቅ አይደለም፡፡ ሁሉን ብቻዬን አደርገዋለሁ አላለም፡፡ አሮንና ሖር እንደሚያስፈልጉት ተቀበለ፡፡ ጎበዝ ሰው እንዲህ ነው፡፡ ሁሉንም ለብቻዬ እችለዋለሁ አይልም፡፡ የአንድ ሰው ውጤታማነት የብዙ ሰዎች አስተዋጽዖ ውጤት ነውና፡፡ ድል የሙሴም፣ የአሮንና የሖርም የየብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ድል የሙሴ፣ የአሮንና የሖር የኅብረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ በፍቅር በህብረት ለድል እጅ ለእጅ እንያያዝ አሜን፡፡

በዚህ እና በሌሎችም ጽሁፎች ተባርከው ከሆነ ገጹን ላይክ ቢያደርጉ አስተያየቶትንም ቢያሰፍሩልኝ ደስተኛ ነኝ አመሰግናለሁ።

ካሱ ቦስተን

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s