ክፍል 1
እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ልባቸውን በዓለም አስቀምጠው ነፍሳቸውን እየተንከባከቡ ባላቸው ላይ እንዲጨመርላቸው ጌታን ለመጠየቅ ወደ የጸሎት ቤቱ የሚጎርፉት ሳይሆኑ ሁሉን ትተው የተከተሉት ናቸው። «በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።» ጌታ ግማሽ ትቶ የተከተለው ደቀ መዝሙር አልነበረውም። ዛሬ ዛሬ ይህ ሁሉን ትቶ ኢየሱስን የመከተልና የርሱ ደቀመዝሙር የመሆን ጥሪ የተለወጠ ወይም የተረሳ ይመስላል። አንዳንዶቻችንም ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ የተቀመጠ መርህ ይመስለናል። ምክንያቱም ሁሉን ትተን፣ የርሱ ደቀመዝሙር ለመሆን ራሳችንን ክደን፣ መስቀላችንን ተሸክመን የህይወትን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለማድረስ ሳይሆን ፡- እኛ እንድንበለጽግ ፣ ከሰው ሁሉ ልቀን እንድንታይ ኢየሱስን የተከተልን ከሆነ ወንጌሉን በጽሑፍ ደረጃ ባንቀይረውም (ያውም አታሚዎቹ ሌሎች ስለሆኑ) በኑሮአችን ግን የተገለበጠ ወንጌል እየኖርን መሆኑ ይታያል። ቃሉ ግን እንዲህ ይላል “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።” ምናልባት ይህን ቃል የምንጠቅሰው አሁንም ከሥጋዊ ምኖቶቻችን አንጻር አስታከን ዳቦ ያበረከተው ጌታ አልተለወጠምና እኔንም ገንዘብ ይሰጠኛል ከሚል መንፈስ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ የማይለወጥ መሆኑን ካመንን ትምህርቱም እንደማይለወጥ እንመን። ያ ሐዋርያቱን «ሁሉን ትታትችሁ ተከተሉኝ» ያለው ክርስቶስ ያ «ማንም ራሱን ቤተሰቡን ሚስቱን ልጆቹን አባቱን እናቱ የማይክድና መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የኔ ሊሆን አይችልም ያለው አሁንም አይለወጥም። የክርስቶስ ኢየሱስን የደቀ መዝሙር መለኪያ ዝቅ አድርገን ልናምንና ልናስተምር በጭራሽ መብትና ስልጣን የለንም።
ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ሁሉ የጠራውና መከተል የሌለባቸውንም የመለሰው በዚህ መለኪያ ነው። ህዝብ በዛ ብሎ ባየ ቁጥር መለኪያውን እንዳላወቁ አውቆ መለስ ብሎ ይነግራቸው ነበር “ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው፦ ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።….. እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” (ሉቃ.14:25) ኢየሱስ ብዙ ህዝብ በማየቱ ብቻ «አገልግሎቴ ብዙ ህዝብ አስገኘልኝ» ብሎ ደስ አላለውም። ይልቅስ የህዝቡ መብዛት ደቀመዝሙር የመሆን መለኪያውን አለማወቃቸው መሆኑን አውቆ ዘወር አለ። እርሱን ለመከተል መክፈል ያለባቸውንም ዋጋ ነገራቸው። ዛሬም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ያለው የህዝብ መብዛት የደቀ መዝሙሮች ብዛት አለመሆኑን የጌታ መንፈስ ያብራልን። ይህም የሆነው ይህንን ኢየሱስ የሰበከውን ብቸኛ ወንጌል ባለመስበካችን ነው። ሌላ ወንጌል ሌላ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም። በውጤቱም ብዙ ህዝብ ቢኖርም ብዙ ደቀ መዝሙር የለም። የእኔነት የጥልና የክርክር ብዛት የመስቀሉ ወንጌል አለመኖር ምልክት ነው። መስቀል ያልተሸከሙ ብዙ ትክሻዎች ጥልን ክርክርን ለመሸከም ተጋልጠዋል።
ዛሬም ጌታ የርሱን ፈለግ በተከተሉ እውነተኛ አገልጋዮቹ ዘወር ብሎ እውነተኛውን የደቀመዝሙር መለኪያ ለህዝቡ እየተናገረ ነውና ስሙት አዎ ብዙ ከመድከማችን በፊት እንስማው። የነርሱ ደቀመዛሙርት እስከሆናችሁና የጸሎት ቤታቸውን ወንበር እስከሞላችሁ ድረስ የኢየሱስ ደቀመዛምርት ትሁኑ አትሁኑ የማይገዳቸው ምንደኛ አገልጋዮች ይህንን አይነግሯችሁም። እውነተኛው ጌታ ግን በከንቱ እንዳትደክሙ ቆም ብላችሁ ኪሳራችሁን እንድታስቡ ዘወር ብሎ እየተናገረ ነው። ጌታ የፈለገው ራሳቸውን ክደውና መስቀላቸውን ተሸክመው፣ ለራሳቸው መኖር አቁመው እርሱ የሚኖርባቸውን ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንጂ የህዝብ ብዛትን አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ይህ ስብከቱ ብዙ ጊዜ ብዙ ህዝብን ወደ ኋላ ቢመልስበትም መንገዱን አልቀየረም። ህጻናትና ሴቶች ሳይቆጠሩ አምስት ሺ ያህል ሰውን እንጀራ አበርክቶ ካበላ በኋላ በነበረው ቀን ያንን አገልግሎት እንዲቀጥልና ቢቀጥል ህዝብ እንደሚበዛለት አስበው ተጠራርተው የመጡትን ሰዎች አሳፍሮ የመለሰበት ያ ታሪካዊ ቀን አንመለስም ያሉ አስራ አንድ ታማኝ ደቀመዛሙርትን ብቻ ይዞ እንዲቀር አድርጎታል።
ዛሬም የምናመልከውና የምናገለግለው ያ ኢየሱስ ከሆነ መንገዱ እንደዚያው ነው። እውነተኛ ደቀመዛሙርት ያልሆኑ፣ ለሚጠፋ መብል፣ ለኑሮ፣ ለብልጽግና ጌታን የሚፈልጉ ሁሉ ወደቤታቸው ሊሸኙ ይገባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጸሎት ቤት በመስራትና ወንበር በማሰራት እንዲሁም ሳምንታዊ ፕሮግራሞችን በማካሄድ ከንቱ ድካም መድከም የለባትም። በእውነት ወንጌል መለኪያ ወደ ቤታቸው ልትሸኛቸው ይገባል። ግን እንዴት እንሸኛቸው? ጸሎት ቤት በር ላይ ቆመን «አትምጡ» ብለን በመመለስ አይደለም ይልቅስ የሚፈልጉትን ምግብ በማሳጣት እንጂ። «ጌታ ይባርከኛል ፣መኪና፣ ቤት፣ ትዳር፣ ገንዘብ ይሰጠኛል» ብለው ሲመጡ ይህንን የሚያሳጣ ወንጌል በመስበክ ነው። ራሳቸውን ክደው መስቀላቸውን ተሸክመው ኢየሱስ ክርስቶስን ራሱን እየበሉና እየጠጡ እንዲከተሉት፣ ኢየሱስ ህይወታቸው እንዲሆን፣ መንፈስና ህይወት የሆነውን ቃሉን በየእለቱ እንዲመገቡ በመርዳት፡- ደቀመዝሙር ያልሆነውንና የኢየሱስ ወንጌል የማያረካውን ህዝብ ከአዳራሾቻችን መቀነስ አለብን።
ካሱ ቦስተን
እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ