እውነተኛ ደቀ መዝሙር

 ክፍል 3

በክፍል 2 ጽሁፌ ላይ በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን መለኪያ እንኳንስ ወደ ኋላ ተመለሱ ሊባሉ ይቅርና «መሪና አገልጋይ ተብለው ሊሾሙ የሚችሉ ሰዎችን ጌታ ኢየሱስ ግን «ለደቀ መዝሙርነት ብቁ አይደላችሁም» ብሎ የርሱን የደቀ መዝሙርነት መለኪያ ያለፉትናና ወደኋላ የተመለሱትን ጥቂት ሰዎች እንመለከታለን ብዬ ቀጠሮ በሰጠኋችሁ መሰረት እነዚህን ሰዎች ማየት እንጀምራለን ለዛሬ አንድ ባለጸጋ ሰው እንመልከት፦ 

ባለጸጋው።

“እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።» ይህ ሰው በዚህ ዘመን ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ውስጥ በ99.9 ከመቶ ተቀባይነት የሚያገኝና ወደ መሪነት ሊደርስ የሚችል ሰው ለመሆኑ ከራሳችን ሌላ ምስክርን አንሻ። 

በመጀመሪያ፦ ሲመጣ ሮጦ ነው የመጣው ይህም ጌታን ለመከተል ያለውን ጉጉት ያሳያል። 

ሁለተኛ፦ «ቸር መምህር ሆይ» ብሎ ነው የጠራው (ኢየሱስ ጌታ ነው ማለቱ ነው)። 

ሶስተኛ፦ እንዲሁ ዝም ብሎ ሳይሆን የቀረበው እየሰገደ ተንበርክኮ ነው። ይህም ለጌታ ክብርን መስጠቱ ነው። 

    ይህ ፍጹም የሆነ መታዘዝና መገዛትን የሚያሳይ የሚመስል አቀራረብ ነው። እንዲህ እያደረገ ወደኛ ወይም ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን የሚመጣን ሰው ደፍሮ ሌላ ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው ይኖር ይሆን? በተለይ ይህ ድርጊቱ በመሪዎችም ላይ ያነጣጠረ ከሆነማ ያለምንም «ይለፍ» ነው ሰተት ብሎ የሚገባው። ኢየሱስ ግን ለርሱ እየተንበረከከና «ቸር መምህር ሆይ» እያለ ወደርሱ የመጣውን ሰው ወደ አባቱና ወደ ቃሉ ነው ያስተላለፈው። ለርሱ ባሳየው የግብዝነት አመጣጥ ሳይሆን በቃሉ መዘነው። ኢየሱስ ሰዎችን የሚመዝነው ሰዎች ለእግዚአብሔር ቃል ባላቸው መታዘዝ ብቻ ነውና። እርሱን ጌታና መምህር እያሉ የአባቱን ፈቃድ የማያደርጉትን አይሻም “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” በማለት አስረግጦ ተናግሮአል። የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም እንጂ ለራሱ ክብርን ሊሻ አልመጣምና። ስለዚህ ቸርና ደግ መምህር እንደሆነ እየተናገሩ የሚመጡትን ሁሉ ወደ አባቱ ፈቃድ ይመራቸዋል። (ማቴ.7፡21 ዮሐ.3:1-3)

ይህ ሰው ለደቀ መዝሙርነት ባልተዘጋጀ ልብ ቸር መምህር ሆይ እያለ ሲቀርብም ያገኘው መልስ እንዲህ የሚል ነበር “ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።” የሚገርም ነው። ይህን ሁሉ ትእዛዝ ከህጻንነቱ ጀምሮ የፈጸመ ሰው ከሆነማ ሌላ ምን ይጠየቃል? መምህሩ ግን ወደደውና የመጨረሻውን ክቡር ጥሪ ጠራው “። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።” ልብ በሉ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን አንድ ነገር ብቻ ነው የቀረው እንግዲህ ያንን ሁሉ ትእዛዝ ከህጻንነቱ ጀምሮ የፈጸመ ሰው አንድ ነገር ይከብደዋል ትላላችሁ? ግን ከበደው። “ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።” ጌታ ቸር መምህር እንደሆነ፣ የዘላለም ህይወት በርሱ እንደሚገኝ አውቆ እንዴት ተመልሶ ይሄዳል? ያለው ኃብትና ብልጽግናስ እንዴት ከኢየሱስ በለጠበት? ይህንን ስናነብ ለመመለሱ ምክንያት ሆኖ የተቀመጠው ብዙ ኃብት ነው ግን የማን ኃብት? የሚለውን መጠየቅ አለብን። አለዚያ ሃብቱን ብቻ እናይና በሃብቱ ውስጥ የተደበቀውን እኔ (እኔነት) እንረሳለን ሃብቱን ከኢየሱስ አስበልጦ ያሳየው ያ በመስቀል ካልሆነ የማይሞተው ማንነቱ ነው። እኔነታችን ካልሞተና መስቀላችንን ካልተሸከምን ኢየሱስን መከተል የማንችለው ለዚህ ነው። አሮጌው ሰው አዳም መስቀልን እንጂ ኢየሱስን አይጠላም መስቀል የሌለው ኢየሱስ ቢያገኝ ኖሮ በጣም ደስ ይለዋል። እርሱ ራስና አዛዥ እንደሆነ ኢየሱስን መከተል ቢችል ከእኔነቱ በስተቀር ሁሉን ለጌታ ሰጥቶ መንፈሳዊ መባልን ይወዳል። አዳም የሚጠላው እርሱን ገድሎ እልቅናውን የሚወስድበትን ኢየሱስ ብቻ ነው። እውነተኛው ኢየሱስ ደግሞ ከመስቀል ተለይቶ አይገኝም። ስለዚህ ኢየሱሰ ወደ እኛ ህይወት ሲመጣ የመጀመሪያ ስራው በመስቀሉ ሥራ አሮጌነታችንን ማስወገድ ነው። 

    የርሱ ቅርንጫፎች የሆኑት ሁሉ ግን በርሱ መወገድ ብቻ ይወገዳሉ። የዛፍ ግንድ ቅርንጫፎቹን ቅጠሉንና ፍሬውን ያመነጨና የተሸከመ የዛፉ ዋነኛ ክፍል ሲሆን ቅርንጫፎቹ ፍሬዎቹና ቅጠሎቹ የግንዱ ወይም የዛፉ ናቸው። እኔነት ደግሞ «የኛ» የምንላቸውን ነገሮች ሁሉ የሚቆጣጠር የሰው ግንዱ ነው። ስለዚህ ሰው ስለማንነቱ ሲጠየቅ «እኔ» ይልና ስላለው ነገር ሁሉ ሲጠየቅ «የኔ» ይላል። እንግዲህ «የኛ» የምንላቸው ነገሮች ሁሉ የተንጠለጠሉት በ«እኔ» ላይ ነው። አንድ ሰው ከላይ እንዳየነው ባለጸጋ እኔነቱን ሳይለቅ በእኔነቱ እንዳለ ሆኖ ብዙ ነገርን ሊያደርግ እግዚአብሔርንም ሊያገለግል ይችላል። 

    ሰው እኔነቱን ሳይለቅ የሚያገኛቸው ነገሮች በሙሉ “የእኔ” ብሎ እንደሚጠራቸው አይተናል። በመሆኑም ሰው እኔነቱ ሳይሞት ኢየሱስን እከተላለሁ ቢል፣ ቸር መምህር ሆይ ብሎ ቢጠራው ፣ሃይማኖተኛ ቢሆን፣ ትእዛዛቱን ለመፈጸም ቢተጋ ይህ ሁሉ ስለ «እኔ» ወይም ለ«እኔ» ነው። ያለውን ሃብት ሁሉ «የእኔ» እንደሚል፡- ሃይማኖቱንም፣ ኢየሱስንም የኔ ብሎ ይቆጥራል፣ ያስባል። ለምን ትእዛዛቱን ይፈጽማል? ራሱን እኔነቱን ስለሚወድ ሲኦል እንዳይገባበት፣ በምድር በብዙ ጥረት ፍላጎቱን አሟልቶለት ያኖረው እኔነቱ ሲሞትም የሰማዩን እንዳያጣ ያስብለታል። በላይ በሰማይ በወርቅ ቤት እንዲኖርና በምድር ሙሉ በሙሉ ያልረካው ማንነቱ በላይ እንዲረካለት መንፈሳዊ ለመሆን ይተጋል። እውነተኛው ክርስትና ግን ኢየሱስን «ለእኔ» መቀበል ሳይሆን «እኔን» ለኢየሱስ ማስለቀቅና «እኔን» በመስቀሉ ገድሎ «በእኔ» ምትክ ክርስቶስን ማኖር ነው። ይህ ገብቶት ክርስቶስን የተቀበለው ሐዋርያ እንዲህ ያውጃል፦ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” (ገላ.2:20)

   ከላይ ያየነውን ባለጸጋ ሰው በዚህ ሚዛን ስናየው ዘመኑን ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሲፈጽም የኖረው ወደ ዘለዓለም ህይወት ለመግባት ለመሆኑ ከጥያቄው እንረዳለን። ችግሩ ያለው የዘላለምን ህይወት መፈለጉ አይደለም። ያንንማ ሁላችንም መፈለግ አለብን። ነገር ግን ይህንን ህይወት ለመውረስ የምንሄድበት መንገድና ይህን ህይወት ለማን እንደፈለግነው አለማወቃችን ላይ ነው። በዚህ ስፍራ ሰውየው ፈልጎ የመጣው የዘላለምን ህይወት ነው። ጌታ ኢየሱስም ለዚህ ሰው የዘላለምን ህይወት የሚያገኝበትን መንገድ ነው የነገረው። እንግዲህ ልዩነቱ ምንድን ነው? ልዩነቱማ ሰውየው የዘላለምን ህይወት የፈለገው «የእኔ» ከሚላቸው እንደ አንዱ የሚቆጥረው፣ በእኔነቱ ስር የሚገዛ፣ «አለኝ» የሚለው የዘላለም ህይወት እንዲኖረው ሲሆን እውነተኛውና ጌታ የሰጠው የዘላለም ህይወት ግን እኔነቱን የሚያጠፋና ከዚያ በፊት እኔነቱ የሚቆጣጠራቸውን ነገሮች ሁሉ አጥፍቶ ክርስቶስን ህይወቱ የሚያደርግ የዘላለም ህይወት ነው። 

የዘላለም ህይወት አሁን እኔነቱ ከያዘው ሃብት ጋር ጨምሮ «የኔ» የሚለው ህይወት ሳይሆን የርሱን እኔነት አጥፍቶ በርሱ የሚኖር ህይወት ነው። ስለዚህ ያለህን ሁሉ ሽጥና መስቀልህን ተሸክመህ ተከተለኝ ተባለ። ባለው ላይ ሊጨምር መጥቶ ሁሉን እንዲያጣ ተነገረው። በዚህም የምንማረው የዘላለም ህይወት ማለት እኔነታችን «አለኝ» ከሚላቸው ነገሮች ጋር ቆጥረን የእኔነታችን ንብረት የምናደርገው ሳይሆን እኔነታችንና «የኔ» የምንለውን ሁሉ ትተን የምናገኘው ክርስቶስ ነው። “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።” (ማቴ.16፡25) በዚህ ቃል መሰረት ይህ ሰው የተጠየቀው ነፍሱን ያገኛት ዘንድ እንዲያጠፋት ነው። እርሱ ግን ሊያድናት ስለወደደ አጠፋት። እንግዲህ ቃሉን በሚገባ ስንረዳው ሰውየውን ወደኋላ የመለሰው ኃብቱ ሳይሆን እኔነቱ ነው። ኃብቱ የእኔቱ ስለሆነ እኔነቱና ሃብቱ ደግሞ መስቀል ካልተሸከመ በቀር የማይለያዩና የተጋቡ ስለሆኑ፡ መስቀል መሸከምን የጠላው እኔነቱ በኃብቱ አመካኝቶ መለሰው። እኔነቱ መስቀሉን ቢሸከም ኖሮ ግን ኃብቱ በርሱ ላይ አቅምን ያጣል። እኔነት የለውምና ምኑን ይዞ ይጎትተዋል? እንግዲህ ይህ ሰው እኔነቱን ሳይክድና መስቀሉን ሳይሸከም ይህን ያህል አስገራሚ መንፈሳዊ ጉዞ መጓዙ አዳም ለምድር ብቻ ሳይሆን የዘላለምን ህይወትም በወዙ ለማግኘት እስከ መስቀል ጥግ ድረስ መሄዱ እንደማይቀር እንድንገነዘብ ይረዳናል። ህይወትን የምናገኝበትና የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የምንሆንበት መንገድ መስቀልን ተሸክሞ ኢየሱስን መከተል ብቻ መሆኑ ግን ሌሎች ትጋቶቻችን ሁሉ ከመስቀሉ ወዲህ ያሉ ከንቱ የአዳም ጥረት አድርጎአቸዋል። ይገርማል በዚህ ሰው ልብና አስተሳሰብ ሆነን ትእዛዛቱን ሁሉ ፈጸምን ብንል እንኳ መስቀሉን ተሸክመን ኢየሱስን ካልተከተልን እንደዚህ ሰው እያዘንን ከመመለስ በቀር ሌላ ምርጫ የለንም። ጌታ ከዚህ ያነሰ መለኪያ የለውምና። እርሱስ ተፈጸመ ያለው በመስቀል ላይ አይደል? እኛ መስቀሉን ሳንሸከምና አሮጌ ማንነታችን ሞቶ ክርስቶስ በኛ ሳይኖር ከመስቀሉ ማዶ ሆነን ተፈጸመ (ሁሉን ፈጽሜአለሁ) ማለታችን ለምን ይሆን? ዛሬ ለኛ መለኪያው የተቀነሰ ይመስል ከዚህ ሰው እንኳ ያነሰ ምልልስ እየተመላለስን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመባል መድፈራችን ግን የመጽሐፍ ቅዱሱን ኢየሱስ እጅግ አሳዝኖታል። ቢወደንም ከርሱ ጋር የምንሆንበትን መንገድ አበክሮ ከመናገር አላቋረጠም። እርሱም “መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው መጣራቱ ነው። ቀጣዩን ደግሞ በክፍል 4 እናነባለን ይጠብቁን።

ካሱ ቦስተን

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s