እውነተኛ ደቀ መዝሙር

ክፍል 4

ባለፈው ክፍል 3 ጽሁፍ እንዳየነው ባለጸጋው ሰው የጌታ ደቀመዝሙርነትን መስፈርት ማሟላት አቅቶት ሲመለስ አይተን ለዛሬ ሌላ ሰው ለማየት ተቀጣጥረን ነበር ይህንን ሰው ደግሞ እንመለከታለን አብረን እናንብበው።

አንድ ሰው

“እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።(ማቲ 8፤19-20)” 

   ኢየሱስ ለሰዎች የሚመልሰው በአፋቸው የተናገሩትን በመስማት ብቻ ሳይሆን በልባቸው የነበረውንም አሳብ ያውቅ ስለነበር ከዚያ በመነሳት ትክክለኛና አፋቸውን ሳይሆን ልባቸውን የሚመጥን መልስ ነው የሚነግራቸው። ሰለዚህ ብዙ ጊዜ የጠያቂዎችን የውስጥ ፍላጎትና ምኞት እንዲሁም ትክክለኛ ማንነታቸውን የምናገኘው በሰዎቹ ጥያቄ ሳይሆን በኢየሱስ መልስ ውስጥ ነው። 

    ይህ ሰው ኢየሱስ ወደሚሄድበት ሁሉ መከተል ነው የፈለገው። ነገር ግን ኢየሱስ እያደረገ የነበረውን ተአምራትና የሚከተለውን ብዙ ህዝብ ስላየ በልቡ ከኢየሱስ ጋር ከሄደ ምንም እንደማይቸገር አስቦአል። ይህን አሳቡን ያወቀው ጌታ እርሱን ከመከተሉ በፊት ራሱን እንዲክድ መጠየቁ ነው። ምክንያቱም መኖሪያና መተዳደሪያን ተስፋ አድርጎ ወይም ከኢየሱስ ጋር ከሆንኩ አልቸገርም ብሎ ኢየሱስን መከተል ራስን አለመካድ ነውና። ስለዚህ ኢየሱስ ለዚህ ሰው ምንም ነገር ከእርሱ ጠብቆ (ማለትም አንድ ነገር አገኛለሁ ብሎ እንዳይከተለው) የርሱ ኑሮ ከሰማይ ወፎችና ከምድር ቀበሮዎች ያነሰ እንደሆነ አሳየው። ራሱን ካልካደ በቀር ከሰማይ ወፎችና ከምድር ቀበሮዎች ያነሰን ኑሮ የሚኖር ሰው እንዴት ሊከተል ይችላል? 

ለመሆኑ እኛ እንደዚህ አይነቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ነው እየተከተልን ያለነው? ወይስ ሰዎች በምኞታችንና በፍላጎታችን ልክ በአእምሮአችን የሳሉብንን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ኢየሱስ? 

    ብዙዎች የሚከተሉትን ኢየሱስ ሲናገሩ ስሰማ ምንም መከራ እንዳያገኛቸው የሚንከባከባቸውን፣ ከጎረቤቶቻቸው ሁሉ ይልቅ ያበለጸጋቸውን፣ የተመኙትን ሁሉ አንድም ሳያስቀር የፈጸመላቸውን ኢየሱስ ነው። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር እንዲህ ነው ያለው “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ.16:33) በዚህ መንገድ እየተራመደ የነበረው ሐዋርያም “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።” በማለት ያውጃል። (ሮሜ.8፡35) በሌላም ስፍራ “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤” በማለት ቅዱሳንን ያጽናናል። (ፊል.1፡29) 

    እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ከሆንን ክርስቶስ በሥጋ በዓለም ሳለ ከኖረው ኑሮና ከተመላለሰበት ምልልስ የተለየ ልንንኖር አንችልም። እርሱን ያሰቃየችና ያሳደደች ዓለም እኛን በመልካም ተቀብላ ባለጸጎችና ሁሉ የተመቻቸው ካደረገችን ግን የኢየሱስ ተከታዮች አይደለንም። ይህንንም ጌታችን አስረግጦ ሲናገር “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።” ብሎአል (ዮሐ.15፡18) አዎ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። 

    በዚህ ቃል መለኪያ ዛሬ በምድር ላይ ክርስቶስ ያልኖረውን ምቹ ኑሮ የሚኖሩና በወንጌል ስም በከፈቱት ንግድ በልጽገው ያሉ ሁሉ ከጌታቸው መብለጣቸው ነው ወይስ ባሪያ አይደሉም? ባሪያስ ከጌታው አይበልጥም ባሪያ ባይሆኑ ነው እንጂ። ይህን ስንል መከራን ወይንም ማጣትን ጠርተን እናመጣዋለን እያልን ሳይሆን በምንሸከመው መስቀልና በተከተልነው መምህር ውስጥ የተካተቱ ስጦታዎች ናቸው። ማንም ክርስቶስን ሰብኮ የማይሰደድ በብዙ መከራና ስቃይ የማያልፍ የለም። ” በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2.ጢሞ.3፡12) ተብሎ ተጽፎአልና። ሁሉም እጁን ዘርግቶ ከተቀበለንና ካልተሰደድን ግን መልሱ ግልጽ ነው በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰል አልተመላለስንም። መመላለስ በጀመርንበት ቅጽበት ግን ስደቱ መከራው ያን ጊዜውኑ ይጀምራል። እንግዲህ ይህንን ከላይ ያየነውን ሰው የጠራው ኢየሱስ ምንም የሌለው ኢየሱስ ነው። ራሱን ኢየሱስን ወዶ ካልሆነ 

«ኢየሱስ አንድ ነገር ይሰጠኛል» ብሎ ሊከተለው እንዳይሞክር ምንም እንደሌለው ገልጾ አሳየው። ያመንከው ኢየሱስ ይህንን ነው? ከሆነ መልካም።  

    እንግዲህ ኢየሱስን መከተል ወይም ደቀመዝሙር መሆን ሌላ ምንም ሳይፈልጉ ኢየሱስ እንደኖረና እንደተመላለሰ መኖር ብቻ ነው። ይቀጥላል።

ካሱ ቦስተን

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s