እውነተኛ ደቀ መዝሙር

ክፍል 5

በዛሬው ክፍል ንባባችን ደግሞ የጌታ ደቀመዝሙርነትን መስፈርት ማሟላት አቅቶት እናትና አባቱን ለመቅበር ስለተመለሰ አንድ ሰው እንመልከት ፦

አባቴንና እናቴን ልቅበር

“ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ።” (ሉቃ.9፡59)

የዚህን ሰው ምክኒያት ስንመለከት ይህስ በጣም አሳማኝ ምክንያት ነው ብለን እንል ይሆናል። ለዚህስ ፈቃድ የሚከለክል ማን ሊኖር ይችላል? በጣም ክፉ የተባለ አለቃ ቢኖረን እንኳ ለዚህስ ልቡ ይራራል። እንዲያውም ከቻለ ራሱም ቀብሩ ላይ ሊመጣ ይሞክራል እንጂ፡ ኢየሱስስ? ኢየሱስማ ለደቀመዝሙር የተቀመጠውን መለኮታዊ መለኪያ ለቀብር ብሎ አይሽርም። ምንም ነገር ከደቀመዝሙርነት በልጦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ሊኖር አይችልም። 

   ኢየሱስን ከመከተላችን በፊት ልናደርገው የሚገባ ምንም ነገር የለም። ስለዚህ መምህሩ እንዲህ መለሰለት “ኢየሱስም፦ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው።” በእውነተኛው ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት ከሁሉ ትበልጣለች። ለሙታን ህይወት የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን መንግስት ምንም ነገር ከማይሰጡ ነገሮች ጋር ልናወዳድረው አይገባንም። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ ስለ አንድ ጊዜ ክስተት ብቻ ሳይሆን አንድ ደቀመዝሙር በዘመኑ ሁሉ መከተል ያለበትን መርህ ነው ያስቀመጠው። 

    ምናልባት እንደሰው አስተሳሰብ ይህ ሰው ዘመኑን ሁሉ ጌታን ሊከተል ከሆነ አንድ ጊዜ ሄዶ እናቱንና አባቱን ቀብሮ ጣጣውን ጨርሶ ቢመጣ ምን አለበት? እንል ይሆናል። ነገር ግን ይህ ጥያቄ የአንድ ጊዜ ክስተትን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን ሰውየው ለነገሮች የሚሰጠውን ቅደም ተከተልና በህይወቱ ሁሉ የሚጠቀምበትን የህይወት ሚዛን የሚያሳይ ነው። ዛሬ እናት አባቱን መቅበር ኢየሱስን ከመከተል የሚቀድም ሆኖ ከታየው ነገም ሌላ ችግር ሲገጥመው አንገብጋቢውንና ዋናውን የእግዚአብሔር አጀንዳ ትቶ ይሄዳል። በህይወቱ ሁልጊዜ ከመንግስቱ ሥራ ይልቅ በሰዎች ዘንድ የተለመደው የኑሮ ሥርዓት እና ማህበራዊ ህይወት ይቀድምበታል። እነዚህ የማህበራዊ ኑሮ ክስተቶች ደግሞ እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሚያቋርጡ አይደሉም። አንድ ሲሄድ አንዱ ይመጣል። ዛሬ አባቴንና እናቴን ልቅበር ያለው ሰው ነገ አጎቴንና አክስቴን ከነገ ወዲያ ደግሞ ሚስቴንና ልጄን እያለ እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ በምክንያት ገመድ ወደ ኋላ እየተጎተተ ይኖራል። ስለዚህ ኢየሱስ እዚህ ጋ እያፈረሰ ያለው የሰውየውን አስተሳሰብ ነው። ኢየሱስ በመልሱ ውስጥ አንድ ሁላችንም በቅጡ ልንረዳው የሚገባንን ሚስጢር ገልጦአል። ይህም ማን ምን መስራት እንዳለበት ማወቅ እንዳለብን ነው። ይህ ሰው እርሱ ሊሰራው የማይገባውን ነገር ነበር ለመስራት የጠየቀው። በዚህም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሊሰራው የማይገባውንና የሚገባውን ነገር አስቀድመን ማወቅ እንዳለብን እንረዳለን። 

    ለምን ደቀ መዝሙር እንደሆንንና ደቀ መዝሙር ሊሰራ የሚገባውን፣ ካላወቅን ደቀመዝሙር መሆን አንችልም። ደቀመዝሙር ያሰኘን አንዱን ጌታ ብቻ መከተላችንንና እርሱ የመጣበትን ዓላማ ለማስፈጸም መጠራታችን ነው። የደቀመዝሙር ሥራ ጌታው ክርስቶስ ህይወቱን የሰጠበትን የመንግስቱን ወንጌል መስበክንና ሰዎችን ወደ ህይወት ማምጣት ሲሆን የሙታን ሥራ ደግሞ ሙታናቸውን መቅበር ነው። እንግዲህ ይህ ሰው ሙታንን ለመቅበር በመጠየቁ ከማን ወገን መሆኑን አረጋግጦአልና የኢየሱስ ደቀመዝሙር ሊሆን አይችልም። ሙታን የተባሉት ማለትም በበደላቸውና በኃጢአታቸው ሙታን የሆኑት ሙሉ ጊዜአቸውንና ኃይላቸውን ጥበባቸውን የሚያውሉት የእግዚአብሔር መንግስት አጀንዳ ያልሆነ የራሳቸውን ሙት ስርዓት ለማስፈጸም ነው። ዓለም ይህንን የሙታን ስርዓት ለማስፈጸም በሚችል በጣም ብዙ ህዝብ ተሞልታለች። አብዛኛው የዓለም ህዝብ ሙት እስከሆነ ድረስ የፖለቲካውን አመራር የሚመሩ፣ አገር የሚያስተዳድሩ፣ የሚነግዱ ብዙዎች ናቸው። እቁቡ፣ እድሩ፣ ቀብሩ፣ ፓለቲካው ፣ንግዱ፣ በእልፍ አእላፍ ሙታን የተሞላ ነው። ሁሉም ሲታይ ሰዎች እጅብ ብለውበታል። የሞተ ሰው ስለመቅበርም ቢሆን ከዘመን ለውጥና ከብዙ የሥራ ውጥረት የተነሳ እንደ ድሮው ለነፍሴ ብሎ የሚቀብር እየመነመ ቢመጣም ራሱን የሚቀብረው እንዳያጣ የሚፈራ ሁሉ በተለያየ ስም በመደራጀት ሲያከናውን ይታያል። ይህ እንግዲህ በሙታን በተሞላችው ዓለም የሚታየው ሁኔታ ነው። 

      በሌላው ጎራ ደግሞ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የተጠሩ ጥቂት የጌታ ደቀመዛሙርት የአለም ብርሃን ለመሆንና ለዚህች በሙታን ለተሞላች አለም የክርስቶስን ህይወት ለማድረስ የተሰበሰቡ አሉ። በአለም ካለው ህዝብ ጋር እነዚህን ስናያቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። የያዙት ዓላማ ግን ሙታኑ ከያዙት ጋር የማይነጻጸር ፈጽሞ የተለየ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳንን የሚሰጥ የመንግስቱን ወንጌል ነው። በሙታኑ ጎራ ብዙ ትጉ ሰራተኞች ቢኖሩም በህያዋኑ ጎራ ያሉት ግን ጥቂቶች በመሆናቸው “የመከሩ ጌታ ሰራተኞችን እንዲልክ ጸልዩ ተብለናል። 

ነገሩ እንዲህ ግልጽ ከሆነልን በክቡር ጥሪ ተጠርቶ ወደ ጥቂቶች ጎራ የገባ የኢየሱስ ደቀመዝሙር ብዙሃኑን ሙታን ለመርዳት ወደእነርሱ ይሻገር ዘንድ አይሆንለትም። እነርሱ በጣም ብዙዎች ናቸው። ዓላማቸውም ያንን የሞተ ሥራ ብቻ መፈጸም ብቻ ነው እንጂ የእግዚአብሔር መንግስት አይደለም። ስለዚህ ሙታናቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ትተን የመንግስቱን ወንጌል እንሰብክ ዘንድ ይገባናል።  ይቀጥላል፤ 

ካሱ ቦስተን

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ ።

One Comment

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s