የዘላለም ሕይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 2

የእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ !

የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ? በሚለው ርዕስ ስር 10 ክፍሎች ያሉትን የመጀመሪያውን ክፍል 1 ን አግኝተው እንዳነበቡ እርግጠኛ ነኝ ካላነበብቡት ግን ይህንን ጽሁፍ ከማንበብዎ አስቀድመው የክፍል 1 ሃሳብን አንብበው ይህንን ክፍል 2 ን እንዲቀጥሉ ከአደራ ጋር እጠይቅዎታለሁ። በዛሬው ጽሁፌ ላይ የእግዚአብሄር ማስጠንቀቂያ የሆነውን ሃሳብ ከመጽሃፍ ቅዱሳችን ላይ እንመልከት፦

ሁሉን የሚያውቅ አምላካችን ክርስቶስ በፍርድ ቀን ብዙዎች እንደሚጠፉና ጥቂቶች ብቻ እንደሚድኑ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ማቴዎስ 7፡13-14 እንዲህ ይላል፡- ‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው›፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባ ነገር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት በርካቶቹ የአለማችን ሕዝቦች መንግስተ ሰማይን አይወርሱም፡፡ እነዚህ ሰዎች በሰፊው ጎዳና ወደዘላለም ጥፋት የሚሄዱ ናቸው፡፡ ይህንን ማስጠንቀቂያ ያለማመቻመች ልንቀበለው ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንዳለው የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው፡፡

ለመሆኑ ጥቂት ሲባል ምን ያህል ነው? በ 1ጴጥሮስ 3፡20 ላይ እንዲህ ተጽፏል፡- ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፣ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም››፡፡ በኖኅ ዘመን ምድራችን ላይ እስከ ሁለት መቶ ሚሊዮን ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ይገመታል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከጥፋት ውሃ መትረፍ የቻሉት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ይህ አስደሳች ቁጥር አይደለም፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ በ 2ጴጥሮስ 3፡9 ላይ ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል›› ቢልም፣ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 7፡13-14 ላይ ስለዘላለም ሕይወት ሲናገር ድነት የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ይናገራል ‹‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው››፡፡ የተቀሩት በርካታዎቹ፣ የዘላለም ሕይወታቸውን እሳቱ በማይጠፋበት ገሀነም ያጠፋሉ፡፡

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሱ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ብቻ ወደ መንግስተ ሰማይ ያደርሰናል፡፡ እኛ የሰው ልጆች በአሁኑ ሰአት ከሁለቱ በአንዱ መንገድ ላይ እንገኛለን፡፡ አንድ ነገር ልጠይቅዎትና እርሶ በየትኛው መንገድ ላይ እንዳሉ ያውቃሉ? ምርጫው የእርሶ ነው፡፡ ነጻ ፈቃድ አሎት፡፡ ከእንስሳት ከሚለይዎት ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነጻ ፈቃድዎ ነው፡፡

እግዚአብሔር ማንም እንዳይጠፋ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ምርጫውን ግን ለእኛ ሰጥቷል፡፡ 2ጴጥሮስ 3፡9 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል››፡፡  1ጢሞቴዎስ 2፡4 ስለ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው››፡፡ እንግዳው ለመዳን በእጃችን ላይ ያለውን ውሳኔ እንጠቀም፡፡ድነትን ለማግኘት ስለ ድነት ትክክለኛ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው› የዮሐንስ ወንጌል 8፡32፡፡ ለመሆኑ አርነት የሚያወጣን እውነት ምንድን ነው? በዮሐንስ ወንጌል 17፡17 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሮ እናገኛለን፡- ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው››፡፡ ስለዚህ ወደ መንግስተ ሰማይ እንድንገባ አርነት የሚያወጣን እውነት ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡መቼም በቤትዎ መጽሃፍ ቅዱስ እንዳለና እያነበቡት እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአት ምን እንደሆነና መዘዙን ሁሉ አስፍሮልናል። በሚቀጥለው ክፍል 3 ጽሁፌ ላይ ኃጢአት የሚያመጣቸውን መዘዞች ይዤልዎት እመጣለሁ እስከዚያው ሰላም ቆዩኝ፡፡

ይህንን ጽሁፍ ካነበቡ በኋላ ለአንድ ወዳጅዎ ማካፈልዎትን አይርሱ አስተያየትና ጥያቄ ካለዎት በሃሳብ መስጫው ላይ ያስፍሩ፤ አመሰግንዎታለሁ።

ካሱ ቦስተን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s