የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 3

ኃጢአትና መዘዙ

ባለፈው ክፍል 3 ጽሁፌ ላይ የእግዚአብሄርን የማስጠንቀቂያ ሃሳብ አስፍሬ እንዳነበባችሁት እርግጠኛ ነኝ፤ ካላነበቡት ግን ያንን አንብበው ወደዚህ ክፍል እንዲሻገሩ እጠይቅዎታለሁ። በዛሬው ጽሁፌ ኃጢአት ያመጣብንን መዘዝ እና እንዴት ከእግዚአብሔር እንደለየን እንመለከታለን፡፡ 

ኃጢአት ከእግዚአብሄር እንዴት እንደለየን መጽሃፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 59፡2፣ ‹‹ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል››፡፡ ብሎ ይነግራናል፤ ከእግዚአብሔር የለየን ኃጢአት ነው፡፡ ሮሜ 3፡23 እንዲህ በማለትም ይህንን ሃሳብ ያጸናልናል ፡- ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል››፡፡ በዚህ ምድር ላይ ከኖረ ሰው ኃጢአት ያልሰራ ጌታችን ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችን ድነት ያስፈልገናል፡፡ 1ዮሐንስ 1፡8 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም››፡፡ ሰው እራሱን በማሳት የኃጢአት ችግር የለብኝም ሊል ይችላል፡፡ ይህንን ሲል ግን ምን እያለ እንደሆነ 1ዮሐንስ 1፡10 ያሳየናል፡- ‹‹ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም››፡፡ እግዚአብሔር፡- ሁሉ ኃጢአት ሰርተዋል ሲል ሁሉም ሰርተዋል ማለት ነው፤ ያ ማለት እኔ አንተ አንቺ ሁላችንም ማለት ነው፡፡ ኃጢአት ከሰራን ይህ የሰራነው ኃጢአት ያስከተለብን መዘዝ አለ። 

ሮሜ 6፡23 የኃጢአት መዘዝ ምን እንደሆነ ይነግረናል፡- ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው›››፡፡ ሞት መለየት ማለት ነው፡፡ በአካል ስንሞት አካላችን በመቃብር ጉድጓድ ውስጥ ሲቀር ነፍሳችን ግን ወደሰራት አምላክ ትሄዳለች፡፡ የመክብብ መጽሐፍ 12፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ››፡፡ በአካላዊ ሞት ነፍስ ከስጋ ትለያለች፡፡ ይህች ነፍስ ታዲያ ወደፈጣሪዋ ስትመለስ በምድር ላይ በስጋ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በሰራችው ኃጢአት ምክኒያት የዘላለም መኖሪያዋን አዘጋጅታ ነውና የመጣችው ወደዚያው ወደዘላለም መኖሪያዋ ትጓዛለች። በክፍል ሁለት ላይ ወደ ዘላለም መኖሪያ የሚያደርሱ ሁለት መንገዶች እንዳሉና አንዱ ወደ ገሃነም (ወደ ዘላለም ሞት) አንዱ ደግሞ ወደ መንግስተ ሰማይ (ወደዘላለም ህይወት) የሚያደርስ እንደሆነ ሁለቱም ደግሞ ወደሚሄዱበት ስፍራ ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ልዩነቱ ግን አንዱ ገሃነም አንዱ መንግስተ ሰማይ መሆኑን አይተናል። ሲዖል ሁሌም የእሳት ባህር ያለበት ስፍራ እንደሆነና የሁለተኛው ሞት ያገኛቸው ነፍሳት የሚሄዱበትን ስፍራ መጽሃፍ ቅዱስ በራዕይ 20 ላይ ይገልጽልናል።        

በሮሜ 6፡23 ላይ ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው››፡፡ እንደሚል አይተናል፡፡ ይህ ሞት ግን መንፈሳዊ ሞት ነው፡፡ ይህም ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተለዩ ሰዎች አድራሻቸው ገሃነም ይባላል፣ ራዕይ 21፡8፡- ‹‹ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው››፡፡ ይህ ሁለተኛ ሞት ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይቶ መኖር ማለት ነው፡፡

ታዲያ ከዚህ ለዘላለም ከእግዚአብሄር የተለየነውን ወደ እግዚአብሄር እንድንቀርብ መፍትሄው ምንድነው ? ይህንን ጥያቄ ክፍል 4 ላይ እንመለከተዋለን እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

ጽሁፉን አንብበው ላይክ የሚለውን ከተጫኑ እና ፎሎው ካደረጉ አዳዲስ ጽሁፎች ሲለጠፉ ወዲያውኑ ያገኛሉ፤ ለሌሎችም ማካፈል አይርሱ። 

ሃሳብ አስተያየት እንዲሁም ጥያቄ ካለዎት በአስተያየት መስጫው ላይ ያስፍሩ አመሰግናለሁ። 

ካሱ ቦስተን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s