የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 4

የእግዚአብሄር መፍትሄ

ባለፈው ክፍል 3 ላይ የሃጢያት መዘዙን አይተናል በዛሬው ክፍል 4 ላይ  ለሰው ልጆች  የኃጢአት ችግር እግዚአብሔር መፍትሄ ያዘጋጀበትን እውነት እናያለን፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነው፡፡ ዮሐንስ 3፡16፣ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና››፡፡ ነፍስን ለሌላው አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ምን ሊሆን ይችላል?

እግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ሳይሆን ጻድቅ ፈራጅም ነው፡፡ ዮሐንስ 5፡30፣ ‹‹እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና››፡፡ ፍትህ በኃጥኡ ላይ ይፈርዳል፡፡ ለአብነት የሚከተለውን እንመልከት፡- ባንክ ስዘርፍ ተገኝቼ ለፍርድ ወዳጄ የሆነ ዳኛ ፊት ቀረብኩ እንበል፡፡ ይህ ዳኛ ወደእርሱ ከጠራኝ በኋላ የክስ ወረቀትህን እቀደዋለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ ከፍርድ ነጻ ነህ፤ ውጣ፤ ቢለኝ፣ ጻድቅ ፈራጅ ያሰኘዋል? ፈጽሞ! እግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅ ነው፡፡

አግዚአብሔር ሕግ ሰጠ፣ የሰው ልጅ ተላለፈው፣ ፈጣሪም የጽድቅ ፍርድ አስተላለፈ፡፡ ይህም ፍርድ ሞት ይባላል፡፡ የሰው ልጅ በሞት ፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ ለበርካታ አመታት በምድር ላይ የስቃይ ኑሮ መግፋት ጀመረ፡፡

ይህን ፍርድ ያስተላለፈው አምላክ ጻድቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ በመሆኑ፣ ከእስትንፋሱ የተካፈለው ሰው በምድር ላይ ሲሰቃይ ማየት አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክኒያት ጻድቅ ፈራጅነቱንና የፍቅር አምላክነቱን አዋህዶ የሚያሳይ ሌላ የድነት መንገድ ለሰው ልጅ አዘጋጀ፤ ይህ የድነት መንገድ ጽንፍ የሚመስሉትን የአምላክ ሁለት ባሕሪያት (ፍርድና ምሕረት) በአንድ መስመር ያገናኘ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያሳለፈው ሊታጠፍ የማይችል የሞት ፍርድ ሳይቀለበስ የሰው ልጅ ከተቆጣው አምላኩ ጋር ታረቀ፡፡ የአገራችን የእምነት ሊቃውንት ይህንን ሁኔታ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ “እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ተጠበበች፡፡” የዚህ አስገራሚ ትእይንት ጀማሪና ፈጻሚው ደግሞ ምንም በደል ያልተገኘበት ኢየሱስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በኢየሱስ ላይ አሳረፈው፤ ፍርዱን አሳየ፡፡ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞቹ ስለ እኛ ሞተ፡፡ በእርሱም ምክኒያት የሰው ልጅ ምኅረትን ተቀበለ፡፡ ከፈጣሪውም የፍርድ ቁጣ ተረፈ ‹‹ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን›› (ሮሜ. 5፡9)፡፡

እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ብቻ ሳይሆን የበቀል አምላክም ጭምር ነው፡፡ ዕብራዊያን 10፡30-31 እነዲህ ይላል፡- ‹‹በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም። ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው››፡፡ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን በፍቅር አምላክነቱ ብቻ ማወቅ ይሻሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ በፍርድ ቀን ሁሉ ሰው በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ እንዴት ያለ አስፈሪ ነገር እንደሆነ ያውቃሉ፡፡

ኢየሱስ መሞት ለምን አስፈለገው? ምክኒያቱም እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ብቻ ሳይሆን ጻድቅ ፈራጅም ጭምር ስለሆነ፡፡ ፍትህ ከፍርድ ውጪ ሊታሰብ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ የኃጥኡን ኃጢአት እንዴት እነደሚያነጻ ገልጿል፡፡ ለኃጢአታችን መንጻት ይህንን መንገድ ልንከተል ይገባል፡፡ ዛሬም ኩነኔ ያለባቸው ሁሉ ይህን የእግዚአብሔር መንገድ ያልተከተሉቱ ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህም ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ የሚሆንባቸውን 2ተሰሎንቄ 1፡8-10 እንዲህ በማለት ይገልጽልናል፡- ‹‹እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፣ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ››፡፡

እግዚአብሔር የጸጋ አምላክም ጭምር ነው፡፡ ጸጋ ለማይገባቸው ሰዎች የተሰጠች የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነች፡፡ ሮሜ 3፡23-24 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል››፡፡ ሁላችን ኃጢአትን አድርገናል፡፡ በዚህም ምክኒያት ሁላችን የገሃነም ፍርድ ይገባናል፡፡ ሆኖም ግን እግዚአብሔር በማይገባን ስጦታ (በጸጋ) ማለትም በክርስቶስ ቤዛነት እኛን ሊያድን ወደደ፡፡ ቤዛነታችን ክርስቶስ ነው፡፡ሰው የሚድነው በጸጋው ነው፡፡ በኤፌሶን 2፡8-9 ላይ እንዲህ እናነባለን፡- ‹‹ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም››፡፡ ‹‹በእምነት መታዘዝ›› (ሮሜ 16፡26) በኩል በጸጋ እንድናለን፡፡ ማንም በመልካምነቱ ወደ መንግስተ ሰማይ የመግባት ድፍረት የለውም፤ ምክኒያቱም ሁሉ ኃጢአትን አድርገዋልና፡፡ በጎነታችን ድነታችንን አይገዛልንም፡፡ ድነታችንን ለማግኘት የሚያስችል ፍጹም ሥራ ልንሰራ አንችልም፡፡ ኢሳይያስ 64፡6 ይመልከቱ፡- ‹‹ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል››፡፡ በማናችንም ውስጥ ለመዳን የሚሆን ምክኒያት አልተገኘብንም፡፡ ሁላችንን የሚያድነን የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው፡፡ ይህ የግዚአብሄር ጸጋ እንዴት ነው ያዳነን ? ቀጣዩን በሚቀጥለው ክፍል እናያለን እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

ይህንን መልእክት አንብበው ሲጨርሱ ከታች ያለውን ላይክ የሚለውን ከተጫኑ በኋላ ፎሎው የሚለውን ቢነኩ ቀጣዩ ክፍል ሲለቀቅ ወዲያው ያገኛሉ፤ ሃሳብ አስተያየትዎ አይለየኝ፤ ስለሚከታተሉ አመሰግንዎታለሁ።

ካሱ ቦስተን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s