የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 5

ክርስቶስ ቅጣታችንን ተቀብሎልናል !

ሁላችን ኃጢአትን አድርገናል፡፡ እግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅ ስለሆነ ለኃጢአታችን የሚገባንን ፍርድ ልንቀበል ይገባናል፡፡ ይህም ደሞዝ ሞት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ልጁ ኢያሱስ ክርስቶስ ይህንን ቅጣት በእኛ ፈንታ ተቀብሎልናል፡፡ ሮሜ 5፡6-10 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና››፡፡ ይህን ፍቅር ለመረዳት አዳጋች ነው፡፡

በተጨማሪ 1ጴጥሮስ 3፡18 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ››፡፡ ዳግመኛ ወደ እግዚአብሔር እቅፍ እንድንመለስ ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ ኃጥኣን በሆነው በእኛ ፈንታ መሰቃየት ነበረበት፡፡ ‹‹እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው›› (2ቆሮንቶስ 5፡21)፡፡ ክርስቶስ እኛ ፈጽሞ ልንሰራው የማንችለውን ሥራ ሰርቶልናል፡፡ እዳችንን ከፍሎልናል፡፡ የሰው ልጅ ይህንን እዳ መክፈል ቢችል ኖሮ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ በበደላችን ሙታን ነበርን፣ ነገር ግን ከወደደን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ክርስቶስ በእኛ ፈንታ እንዲሞት በማድረግ የጽድቅ ፍርዱ ሳይዛባ ከሞት አዳነን፡፡

ሰው የሚድንበት ብቸኛ መንገድ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ዮሐንስ 14፡6 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ኢየሱስም፡- እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም››፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንደርስበት መንገድ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪ የሐዋሪያት ሥራ 4፡12 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና››፡፡ በሙሐመድ፣ በቡድሃ፣ በአይሁድንት፣ ወይም በሌሎች በማናቸውም የሃይማኖት ስሞች መዳን የለም፡፡ እኛ በፈጠርነው የክርስትና ሃይማኖት ስርአቶችም ጭምር መዳን የለም፡፡ ድነታችን የምናገኘው እዳችንን በከፈለው በክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

እዳችንን ለመክፈል ክርስቶስ ተሰቃይቷል፡፡ የተቀበለውን መከራ ማሰብ አእምሮችን ፈጽሞ አይችልም፡፡ ክርስቶስ ወደዚህ አለም የመጣው በሞቱ እዳችንን ለመክፈል ነው፡፡ የክርስቶስን ሞት የሚተነብዩ በርካታ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ክርስቶስ ከመሞቱ ከ700 አመት በፊት የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት አንዱ ነው፡- ‹‹እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ›› (ኢሳይያስ 53፡5-6)፡፡ የክርስቶስ ሞት ድንገተኛ አይደለም፣ የሰውን ልጅ ለመቤዠት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ እንጂ፡፡

ክርስቶስ ሁሉን በማወቅ ችሎታው ሊሆንበት ያለውን ሁሉ ያውቅ ነበር፡፡ በማቴዎስ 20፡17-19 እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን፡- ‹‹ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፣ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው››፡፡ ክርስቶስ ያለማንም አስገዳጅነት በፈቃዱ በእኛ ፈንታ ሊሞትልን ወሰነ፡፡

ክርስቶስ በተዋህዶ ሰውም አምላክም ነው፡፡ ሊሆንበት ያለውን ከማወቅ ባሻገር ሥጋ እንደመልበሱ በሞቱ ተጨንቆ ነበር፡፡ ኢየሱስ ከሞቱ ቀን ቀደም ብሎ ባለው ምሽት በጌቴ ሰማኒ የአታክልት ሥፍራ በነበረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በሉቃስ 22፡41-44 እንዲህ እናነባለን፡- ‹‹ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም። አባት ሆይ፥ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ››፡፡ ክርስቶስ በእርግጥም በመስቀሉ ምጥ ነው ያዳነን፡፡

በተጨማሪ በ1ጴጥሮስ 2፡24 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡- ‹‹ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ››፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ሆነን አንድንታይ ክርስቶስ የኃጢአታችንን እዳ መክፈል ነበረበት፡፡ ሰው በዚህ መንገድ ጻድቅ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ሲታይ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የድነት ስጦታ ተቀብሏልና ከዘላለም ፍርድ ይድናል፡፡

የመስቀል ሞት የሰው ልጅ ሰውን አሰቃይቶ ለመግደል ካበጃቸው የስቃይ ፍርዶች አሰቃቂው ነው፡፡ ከዚህ የባሰ የለም፡፡ ጌታችን በዚህ መስቀል ላይ መግለጽ በሚያስቸግር ስቃይና ጣር ለስድስት ሰአታት ቆየ፡፡ እግዚአብሔር እኛን በማዳን ስራ ውስጥ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ቅጣታችንን በመቀበል ስለእኛ ሞተ፡፡ ምን አይነት ፍቅር ነው! እርሶና እኔ ቃሉን ለመታዘዝ ክርስቶስ የከፈለው ዋጋ በቂ ምክኒያታችን አይሆንምን? ስለዚህ የሃጢያታችንን ዋጋ ተቀብሎ የሞተልንን ጌታ አሁን በልባችን አምነን ብንቀበል የዘላለምን ህይወት እናገኛለን። ሌላ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ የእግዚአብሄር ልጅ የመባልን ስልጣን ያገኘንበትም ስለሆነ በቀጣዩ ክፍል እንገናኝ። ቸር እንሰንብት።

ካሱ ቦስተን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s