ክፍል 6
የእግዚአብሔር ልጅ መሆን !
በክፍል 5 ንባባችን ላይ ክርስቶስ ቅጣታችንን እንደተቀበለ ተመልክተናል። ክርስቶስ ስለእኛ ሲል በመስቀል ላይ እስከሞት ድረስ ያደረሰው እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ እናስተውል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ስንመለከተው አንድ የሚያስገኝልን ትልቅ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ነው። በመስቀል ላይ የሞተልንን ጌታ ኢየሱስን አምነን የዘላለም ህይወት ወራሽ ከመሆናችን ጋር የምንወርሰው የልጅነት ስልጣን እንደሆነ በገላቲያ 3፡26-27 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤››፡፡ ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ፍላጎት ቢኖረንም ይህ ሊሳካ የሚችለው በእምነት በኩል እንደሆነ ጥቅሱ ያስረዳል፡፡ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ነው የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን የሚያደርገን፡፡
ዮሐንስ 1፡12-13 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤››፡፡ ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር ልጅነት ስልጣን የተሰጣቸው እነማን እንደሆኑና ከእግዚአብሔር መወለድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የልጅነት ስልጣኑ የተሰጠው ክርስቶስን ለተቀበሉ ሲሆን ይህን የሚያደርጉ አማኞች ከእንግዲህ ወዲያ ፍጥረታዊ ሰዎች ብቻ እንዳልሆኑ ጥቅሱ ያበስራቸዋል፡፡
የእግዚአብሔር ልጅና ቤተሰብ ለመሆን ዳግም መወለድ ይኖርብናል፡፡ ጌታችን በዮሐንስ 3፡3 ላይ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ ያስተላልፍልናል፡- ‹‹ኢየሱስም መልሶ:- እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው››፡፡ በመቀጠል በዮሐንስ 3፡5 ላይ እንዴት ይህ ዳግም ልደት እንደሚከናወን ያስረዳናል፡- ‹‹ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል:- እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም››፡፡
መንግስተ ሰማይን የሚወርሱት የእግዚአብሐር ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ በ1ጴጥሮስ 1፡4 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል››፡፡ በክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር ልጅ ሆነዋል? ይህን ካላደረጉ በእግዚአብሔር ቃል መሰረት በሰማይ ርስት የሎትም፡፡
ወድ አንባቢዬ የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን በሚል ሃሳብ በተከታታይ ከክፍል 1 ጀምሮ እስከዚህኛው ክፍል ድረስ አብራችሁ ስላላችሁ አመሰግናለሁ ቀጣዩን ክፍልም አብረን እንቀጥላለን እስከዚያው ቸር እንሰንብት
ካሱ ቦስተን