መጽሃፍ ቅዱስ በዕብራውያን 12:14 ላይ (ህያው ቃል ከተሰኘው መጽሃፍ ቅዱስ የተወሰደ) “ከማንም ሰው ጋር ተስማምታችሁ በሰላም ኑሩ ቅድስና የተሞላበትንም ህይወት ለመኖር ፈልጉ ምክኒያቱም ያለቅድስና ህይወት ጌታን ማየት ፈጽሞ አይቻልምና ” በማለት ያሰፈረው ቃል ላይ ቅድስና የተሞላበት ህይወት ለመኖር ፈልጉ ሲለን ይህ ሃሳብ ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛችን አድርገን ከተቀበልንበት ጊዜ ጀምሮ ያለውና ወደፊትም የምንኖረው ህይወት በቅድስና ህይወት ይሁን ነው እያለን ያለው።
ቅድስና ከደህንነታችን ቀጥሎ ትልቅ ግምት ልንሰጠው የሚገባ የህይወት ክፍላችን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የበደላችንንና የሃጢዓታችንን ዋጋ ከከፈለ በኋላ በዕምነት ወደ እርሱ ቀርበን የጽድቁ ተካፋይ እንሆን ዘንድ ተጋብዘናል ግብዣውንም ተቀብለን በጸጋው የጽድቁ ተካፋዮች ሆነናል። ይህ ማለት ግን በምድር የሚኖረንን የቅድስናና የጽድቅ ህይወት ፈጽመን አበቃን እንደፈለግን እንኑር ማለት ግን አይደለም ይልቁንም ጀመርነው እንጂ።
ቅድስና በአንድ ቀን አዳር ወይም በአንድ ቀን ጸሎት የምንከውነው ሳይሆን የእድሜ ልክ ልምምድና ኑሮ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባናል። ለዚህ ነው የእግዚአብሄር ቃል “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ” የሚለን በአጭር መንገድ ተጉዘን ቅድስናን አግኝተን ጨርሰነዋል ማለት ሳይሆን ሳንታክት ሳናቋርጥ ዘወትር በጽናትና በትዕግስት የምንፈልገውና የምንፈጽመው ወደተሰጠንም ወደ እግዚአብሄር ክብር የምንተላለፍበት ብቸኛው መንገድ ነውና ሳንታክት በቅድስናና በንጽህና ለመኖር እንፈልግ ብዬ የዛሬውን መልዕክቴን በዚሁ አጠናቅቃለሁ። ተባረኩ ።
ካሱ ቦስተን