የዘላለም ሕይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 2

የእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ !

የዘላለም ህይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ? በሚለው ርዕስ ስር 10 ክፍሎች ያሉትን የመጀመሪያውን ክፍል 1 ን አግኝተው እንዳነበቡ እርግጠኛ ነኝ ካላነበብቡት ግን ይህንን ጽሁፍ ከማንበብዎ አስቀድመው የክፍል 1 ሃሳብን አንብበው ይህንን ክፍል 2 ን እንዲቀጥሉ ከአደራ ጋር እጠይቅዎታለሁ። በዛሬው ጽሁፌ ላይ የእግዚአብሄር ማስጠንቀቂያ የሆነውን ሃሳብ ከመጽሃፍ ቅዱሳችን ላይ እንመልከት፦

ሁሉን የሚያውቅ አምላካችን ክርስቶስ በፍርድ ቀን ብዙዎች እንደሚጠፉና ጥቂቶች ብቻ እንደሚድኑ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ማቴዎስ 7፡13-14 እንዲህ ይላል፡- ‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው›፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባ ነገር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት በርካቶቹ የአለማችን ሕዝቦች መንግስተ ሰማይን አይወርሱም፡፡ እነዚህ ሰዎች በሰፊው ጎዳና ወደዘላለም ጥፋት የሚሄዱ ናቸው፡፡ ይህንን ማስጠንቀቂያ ያለማመቻመች ልንቀበለው ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንዳለው የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው፡፡

ለመሆኑ ጥቂት ሲባል ምን ያህል ነው? በ 1ጴጥሮስ 3፡20 ላይ እንዲህ ተጽፏል፡- ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፣ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም››፡፡ በኖኅ ዘመን ምድራችን ላይ እስከ ሁለት መቶ ሚሊዮን ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ይገመታል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከጥፋት ውሃ መትረፍ የቻሉት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ይህ አስደሳች ቁጥር አይደለም፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ በ 2ጴጥሮስ 3፡9 ላይ ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል›› ቢልም፣ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 7፡13-14 ላይ ስለዘላለም ሕይወት ሲናገር ድነት የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ይናገራል ‹‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው››፡፡ የተቀሩት በርካታዎቹ፣ የዘላለም ሕይወታቸውን እሳቱ በማይጠፋበት ገሀነም ያጠፋሉ፡፡

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሱ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ብቻ ወደ መንግስተ ሰማይ ያደርሰናል፡፡ እኛ የሰው ልጆች በአሁኑ ሰአት ከሁለቱ በአንዱ መንገድ ላይ እንገኛለን፡፡ አንድ ነገር ልጠይቅዎትና እርሶ በየትኛው መንገድ ላይ እንዳሉ ያውቃሉ? ምርጫው የእርሶ ነው፡፡ ነጻ ፈቃድ አሎት፡፡ ከእንስሳት ከሚለይዎት ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነጻ ፈቃድዎ ነው፡፡

እግዚአብሔር ማንም እንዳይጠፋ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ምርጫውን ግን ለእኛ ሰጥቷል፡፡ 2ጴጥሮስ 3፡9 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል››፡፡  1ጢሞቴዎስ 2፡4 ስለ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው››፡፡ እንግዳው ለመዳን በእጃችን ላይ ያለውን ውሳኔ እንጠቀም፡፡ድነትን ለማግኘት ስለ ድነት ትክክለኛ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው› የዮሐንስ ወንጌል 8፡32፡፡ ለመሆኑ አርነት የሚያወጣን እውነት ምንድን ነው? በዮሐንስ ወንጌል 17፡17 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሮ እናገኛለን፡- ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው››፡፡ ስለዚህ ወደ መንግስተ ሰማይ እንድንገባ አርነት የሚያወጣን እውነት ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡መቼም በቤትዎ መጽሃፍ ቅዱስ እንዳለና እያነበቡት እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአት ምን እንደሆነና መዘዙን ሁሉ አስፍሮልናል። በሚቀጥለው ክፍል 3 ጽሁፌ ላይ ኃጢአት የሚያመጣቸውን መዘዞች ይዤልዎት እመጣለሁ እስከዚያው ሰላም ቆዩኝ፡፡

ይህንን ጽሁፍ ካነበቡ በኋላ ለአንድ ወዳጅዎ ማካፈልዎትን አይርሱ አስተያየትና ጥያቄ ካለዎት በሃሳብ መስጫው ላይ ያስፍሩ፤ አመሰግንዎታለሁ።

ካሱ ቦስተን

የዘላለም ሕይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን ?

ክፍል 1

የዘላለም ሕይወታችን

“የዘላለም ሕይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን?” የሚለው ይህ ጽሁፍ 10 ክፍሎች አሉት፡፡ ለዛሬው ክፍል 1 ን ይዤ ቀርቤያለሁ፤ ማንኛውም ጥያቄ ሆነ አስተያየት ቢኖርዎ፣ በአስተያየት መስጫው ላይ ቢያሰፍሩ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቃል እገባለሁ፡፡

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የቀረቡ ሃሳቦች የእኔን አስተሳሰብና ግምት የያዙ ሳይሆኑ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚናገሩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ ሲናገር ልንናገር፣ ዝም ሲል ደግሞ ዝም ልንል ግድ ነውና፡፡ የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ልናደርጋቸው፣ በጽሐፉ በስማቸው የሚጠራቸውንም በግልጽ ልንጠራቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ያነሰ፣ የበዛ፣ ወይም የተለየ ነገር ሁሉ የስህተት ትምህርት ነውና፡፡

ከእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማነስ የተነሳ በተፈጠሩት በርካታ ሃይማኖቶች ምክኒያት በአለም ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ግራ በጋባት ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ሰአት በአለማችን ላይ የተለያየ አስተምህሮዎች፣ የስነ መለኮት ምልከታዎች እና አስተሳሰቦች ያልዋቸው ከ 600 በላይ ቤተ እምነቶች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ በርካታ እምነቶች ‹የእመን› ጥያቄ የሚቀርብላቸው የአለማችን ሰዎች ምን እና ማንን ማመን እንዳለባቸው ለመወሰን ግራ ተጋብተዋል፡፡ አዳኛችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈቃዱ በከፈለው ስቃይና ሞት ለኃጢአታችን ይቅርታ የሚያስፈልገውን ሁሉ አቅርቦልናል፡፡ በፍርድ ቀን ከሰይጣንና ከመላእክቱ ጋር ወደ ወደ ዘላለም እቶን እሳት መጣል አይገባንም፡፡ እናም ለመዳን የወንጌልን እውነት መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ ወንጌል ምንድን ነው? ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል? በዚህ ጽሁፍ ውስጥ እግዚአብሔር በሰማይ ያዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለመውረስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚናገረውን አብረን እናነባለን፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ጥቅሶች በሙሉ ጠመም/ዘመም ባለ የፊደል አጻጻፍና ደማቅ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ለእነዚህ ጥቅሶች ልብዎንና አእምሮዎን ሊከፍቱ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ቃሎች ውስጥ ምን ሊያስተላልፍ እንደፈለገ መግለጥ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱትን እነዚህን ጥቅሶችን ሲያነቡ ለተሰመረባቸው ቃላት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እጠይቅዎታለሁ፡፡

የዘላለም ሕይወት ስለማግኘትዎ እርግጠኛ ነዎት? ይህ ጥያቄ የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ ዋነኛ ጥያቄያችን መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ብንሞት በእርግጠኝነት በቀጥታ ወደ ገነት እንደምንሄድ እናውቃለን? ነፍሳችን ከስጋችን ከተለየች በኋላ ይህን የምርጫ እድል ዳግመኛ የማናገኝበት በመሆኑ ጥያቄውን በቸልታ ልናልፈው አይገባም፡፡ አንድ ቀን፣ ለዚህ ጥያቄ የሰጠነውን ምላሽ ለማወቅ ሁላችን በፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለን፡፡ የሰው ልጅ ሊያስቀራቸው የማይችላቸው ሁለት ነገሮች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሞትና ፍርድ ይሰኛሉ፡፡ ‹‹ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፣›› ዕብራዊያን 9፡27፡፡ ማንም ሰው እነዚህን ነገሮች ሊያመልጥ አይችልም፡፡

ማንም ሰው ስለነገው ቀርቶ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ስለሚሆነው ነገር እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ይህን ጥያቄ ለነገ ልንገፋው አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር በያዕቆብ መልእክት 4፡14 ላይ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቀናል፡- ‹‹…ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።››

ለእኛ አእምሮ ‹‹ትክክል›› እና ‹‹ስህተት›› በሚመስሉን መመዘኛዎች ላይ ተመስርተን የዘላለም ሕይወትን በሚያህል ውድ ነገር ላይ ስህተት መስራት የለብንም፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በስሜቶቻችንም ላይ ቢሆን መመስረት የለብንም፡፡ እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14፡12 ላይ የሚለውን እንመልከት፡- ‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው››፡፡ ለውሳኔዎቻችን ትክክለኛነት ማረጋገጫው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡

ደኅንነታችንን (ድነታችንን) በተመለከተ የግል ግምቶቻችን ምንድን ናቸው? እኛ የምናቀርባቸው ብዙዎቹ ግምቶች እግዚአብሔር በቃሉ ካስቀመጠው እውነታ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያሉንን ግምቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል መፈተሸ ይኖርብናል፡፡ ይህንን በምናደርግበት ወቅት በእኛና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ያሉ በርካታ ልዩነቶችን ማስተዋል እንጀምራለን፡፡ ጌታችን በማርቆስ 7፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ››፡፡ አምልኮአችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያልተመሰረተ ሲሆን ከንቱ ይሆናል። የእነዚህ ሁሉ አደናጋሪ ትምህርቶች ምንጭ እግዚአብሔር ይመስሎታል? ፈጽሞ! 1ቆሮንቶስ 14፡33 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው››፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ለአይሁድ ሸንጎ በሐዋሪያት ሥራ 5፡29 ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡- ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል››፡፡

በመጨረሻው ዘመን የሰውም ሆነ የእኛ አስተያየት ከፍርድ ለማምለጥ ምክኒያት አይሆኑንም፡፡ ከፍርድ የሚያስመልጠን በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ያመነው ነገር ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ፣ ስለ ዘላለም ሕይወት አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በነገረን እውነት አንጻር የምንዳኝበት የፍርድ ቀን ይመጣል፡፡ ፍርድ የሚሰጠው በዚህ መመዘኛ ብቻ ነው፤ ምክኒያቱም ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፣ የዮሐንስ ወንጌል 12፡48 ‹‹በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል››፡፡ (ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ቅ የተወሰደ) ስለዚህ የዘላለም ሕይወትን አስመልክቶ ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በሌለበት የግሉን አስተያየት ቢሰጠን ልንቃወም ይገባል፡፡ ከነፍሳችን በላይ ምን ሊያሳስበን የሚችል ነገር ይኖራል?

የነፍሳችንን ዋጋ በአለም ያለ ምንም ነገር ሊመጥነው እንደማይችል ያውቃሉ? ማቴዎስ 16፡26 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድነው?›› (ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ቅ የተወሰደ) ነፍሳችን ዘላለማዊ ናት፡፡ እናም ይህችን ነፍስ ለዘላለም በእቶን እሳት ውስጥ እንድትኖር ሊያደርጋት የሚችሉ ጉዳዮችን ሁሉ በቸልታ መመልከት ፈጽሞ አይገባንም፡፡

ክፍል 2 ን በሚቀጥለው ጽሁፌ ይዤልዎት እቀርባለሁ እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

ካሱ ቦስተን

መንፈሳዊ ትረካ

የመጨረሻው ትንቅንቅ ቁጥር 2 መንፈሳዊ ትረካ የሚቀጥለው ቅዳሜ በ 2/19/22 ማለዳ ይቀርብላችኋል ቁጥር አንድ ትረካን “kassuboston” ብለው በስልክዎም ሆነ በኮምፒውተር ላይ ጎግል በማድረግ ዩቲዩብ ላይ ገብተው ማዳመጥ ይችላሉ አመሰግናለሁ
ካሱ ቦስተን

ጋብቻ

መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። (ወደ ዕብራውያን 13፥4)

    በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ጋብቻን በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን ነው ያለው በሁሉ ዘንድ ሲል በሴቷም በወንዱም በእስልምናውም በክርስትናውም በማንኛውም የሰው ዘር ሊከበር ይገባዋል ነው የሚለው እንዲሁ እንደቀልድ የሚታይ ነገር አይደለም እንደቀልድ ዛሬ ተገብቶበት ነገ የሚወጣበት እንደዘበት የሚታይ ጉዳይ አይደለም ነው የሚለን ።

  ሌላው ደግሞ ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል (ይህ ሃሳብ ሊተኮርበት የሚገባው ነው) የሚፈጸም የመንፈስ የነፍስ እና የስጋ ጥምረት ያለበት ነው ይህም ጋብቻ በሁለት ተቃራኒ ጾታ መሃከል የሚፈጸም እና ዘለቄታ ያለው በእግዚአብሔር በቅዱሳን መላአክቱና እና  በሰው ፊት የሚደረግ የቃልኪዳን ትስስር ያለበት ስርዓት ነው ።   

  ዛሬ ዛሬ እንደምናየው ግን የጋብቻን ክቡርነት በዘነጉና ጋብቻ እንዴት እንደተጀመረ ባልተረዱ ግለሰቦችና የጋብቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች እንዲሁም የሃይማኖት ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸመው ቅጥ ያጣ እና ስርዓት የሌለው ወንድና ወንድን እንዲሁም ሴትና ሴትን እያጣመሩ ጋብቻን የመሰረቱ የሚመስላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በምድር ላይ ጥፋትን እንጂ መልካም የሆነን ስርዓት እየፈጽሙ ላለመሆናቸው ሊረዱት ይገባቸዋል። እነዚህን ግለሰቦች ደግሞ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላልና   ( … ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 1 ቆሮ 6 : 9-10)

ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ከፈረደባቸው ስርዓቱን እያስፈጸሙ ያሉትም ከዚህ ፍርድ የሚያመልጡበት መንገድ አይታየንም ስለዚህ ይህንን ስርዓት ከማስፈጸም ሊታቀቡ ይገባቸዋል አንላለን።

   ከዚህ የባሰው የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ደግሞ ይህንን ስርዓት መንግስት ስለፈቀደውና በሕግ ስለተደገፈ ብቻ እግዚአብሔር የፈቀደው ያህል በእግዚአብሔር እናምናለን የሚሉና እግዚአብሔርን እናገለግላለን የሚሉ ግለሰቦችና የሃይማኖት ድርጅቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን ያለማሰማታችውና ዝም የማለታቸው ጉዳይ ስርዓቱን ተስማምተው መቀበላቸውን የሚያሳይ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን እንደማይችል እንገነዘባለን። ትንሽ ቆይቶም እነዚሁ ግለሰቦች ስርዓቱን ለመፈጸም ወይም ጋብቻን ለመፈጸም ወደቤተክርስቲያን ቢመጡ የሚሰጣቸው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለብንም ምክንያቱም አስቀድመን የተቃውሞ ድምጻችንን አላሰማንምና ።

   ይህንን ስርዓት እያስፈጸሙ ያሉና ለማስፈጸም ችግር እንደሌለበትና የማያስጠይቃቸው የመሰላቸው ቤተአምልኮዎች ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከአባታቸው ከዲያብሎስ ዘነድ የተላኩ የጥፋት መልእክተኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም ።

     ስለዚህ በማስጠንቀቅም ይህንን ልላችሁ እወዳለሁ ራሳችሁን ብትመረምሩና ከየት እንደወደቃችሁ ብታስቡና ንስሐ ብትገቡ የትሻለ ነው እላለሁ። በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ። ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። (ራእይ 2:18 – 23)

ካሱ ቦስተን 

መንፈሳዊ ትረካ

የመጨረሻው ትንቅንቅ መንፈሳዊ ትረካ ቁጥር 1 ቅዳሜ 02/12/22 ከማለዳው 7:30 ላይ ተለቋል ያዳምጡት ይጠቀሙበታል ይህ ትረካ 38 ክፍሎች አሉት ከቅዳሜ 2/12/22 ጀምሮ በየሳምንቱ ይቀርባል፡ የዩቲዩብ መስመራችንን “kassuboston” ብለው google ላይ ቢፈልጉት በቀላሉ ያገኙታል፤ ሰብስክራይብ የሚለውን ቢጫኑት ትረካውን በየሳምንቱ ማግኘት ይችላሉ። እናመሰግናለን።

ካሱ ቦስተን