ክፍል 1
የዘላለም ሕይወታችን
“የዘላለም ሕይወት እንዳለን እርግጠኛ ነን?” የሚለው ይህ ጽሁፍ 10 ክፍሎች አሉት፡፡ ለዛሬው ክፍል 1 ን ይዤ ቀርቤያለሁ፤ ማንኛውም ጥያቄ ሆነ አስተያየት ቢኖርዎ፣ በአስተያየት መስጫው ላይ ቢያሰፍሩ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቃል እገባለሁ፡፡
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የቀረቡ ሃሳቦች የእኔን አስተሳሰብና ግምት የያዙ ሳይሆኑ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚናገሩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ ሲናገር ልንናገር፣ ዝም ሲል ደግሞ ዝም ልንል ግድ ነውና፡፡ የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ልናደርጋቸው፣ በጽሐፉ በስማቸው የሚጠራቸውንም በግልጽ ልንጠራቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ያነሰ፣ የበዛ፣ ወይም የተለየ ነገር ሁሉ የስህተት ትምህርት ነውና፡፡
ከእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማነስ የተነሳ በተፈጠሩት በርካታ ሃይማኖቶች ምክኒያት በአለም ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ግራ በጋባት ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ሰአት በአለማችን ላይ የተለያየ አስተምህሮዎች፣ የስነ መለኮት ምልከታዎች እና አስተሳሰቦች ያልዋቸው ከ 600 በላይ ቤተ እምነቶች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ በርካታ እምነቶች ‹የእመን› ጥያቄ የሚቀርብላቸው የአለማችን ሰዎች ምን እና ማንን ማመን እንዳለባቸው ለመወሰን ግራ ተጋብተዋል፡፡ አዳኛችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈቃዱ በከፈለው ስቃይና ሞት ለኃጢአታችን ይቅርታ የሚያስፈልገውን ሁሉ አቅርቦልናል፡፡ በፍርድ ቀን ከሰይጣንና ከመላእክቱ ጋር ወደ ወደ ዘላለም እቶን እሳት መጣል አይገባንም፡፡ እናም ለመዳን የወንጌልን እውነት መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ ወንጌል ምንድን ነው? ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል? በዚህ ጽሁፍ ውስጥ እግዚአብሔር በሰማይ ያዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለመውረስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚናገረውን አብረን እናነባለን፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ጥቅሶች በሙሉ ጠመም/ዘመም ባለ የፊደል አጻጻፍና ደማቅ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ለእነዚህ ጥቅሶች ልብዎንና አእምሮዎን ሊከፍቱ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ቃሎች ውስጥ ምን ሊያስተላልፍ እንደፈለገ መግለጥ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱትን እነዚህን ጥቅሶችን ሲያነቡ ለተሰመረባቸው ቃላት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እጠይቅዎታለሁ፡፡
የዘላለም ሕይወት ስለማግኘትዎ እርግጠኛ ነዎት? ይህ ጥያቄ የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ ዋነኛ ጥያቄያችን መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ብንሞት በእርግጠኝነት በቀጥታ ወደ ገነት እንደምንሄድ እናውቃለን? ነፍሳችን ከስጋችን ከተለየች በኋላ ይህን የምርጫ እድል ዳግመኛ የማናገኝበት በመሆኑ ጥያቄውን በቸልታ ልናልፈው አይገባም፡፡ አንድ ቀን፣ ለዚህ ጥያቄ የሰጠነውን ምላሽ ለማወቅ ሁላችን በፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለን፡፡ የሰው ልጅ ሊያስቀራቸው የማይችላቸው ሁለት ነገሮች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሞትና ፍርድ ይሰኛሉ፡፡ ‹‹ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፣›› ዕብራዊያን 9፡27፡፡ ማንም ሰው እነዚህን ነገሮች ሊያመልጥ አይችልም፡፡
ማንም ሰው ስለነገው ቀርቶ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ስለሚሆነው ነገር እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ይህን ጥያቄ ለነገ ልንገፋው አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር በያዕቆብ መልእክት 4፡14 ላይ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቀናል፡- ‹‹…ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።››
ለእኛ አእምሮ ‹‹ትክክል›› እና ‹‹ስህተት›› በሚመስሉን መመዘኛዎች ላይ ተመስርተን የዘላለም ሕይወትን በሚያህል ውድ ነገር ላይ ስህተት መስራት የለብንም፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በስሜቶቻችንም ላይ ቢሆን መመስረት የለብንም፡፡ እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14፡12 ላይ የሚለውን እንመልከት፡- ‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው››፡፡ ለውሳኔዎቻችን ትክክለኛነት ማረጋገጫው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡
ደኅንነታችንን (ድነታችንን) በተመለከተ የግል ግምቶቻችን ምንድን ናቸው? እኛ የምናቀርባቸው ብዙዎቹ ግምቶች እግዚአብሔር በቃሉ ካስቀመጠው እውነታ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያሉንን ግምቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል መፈተሸ ይኖርብናል፡፡ ይህንን በምናደርግበት ወቅት በእኛና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ያሉ በርካታ ልዩነቶችን ማስተዋል እንጀምራለን፡፡ ጌታችን በማርቆስ 7፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ››፡፡ አምልኮአችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያልተመሰረተ ሲሆን ከንቱ ይሆናል። የእነዚህ ሁሉ አደናጋሪ ትምህርቶች ምንጭ እግዚአብሔር ይመስሎታል? ፈጽሞ! 1ቆሮንቶስ 14፡33 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው››፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ለአይሁድ ሸንጎ በሐዋሪያት ሥራ 5፡29 ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡- ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል››፡፡
በመጨረሻው ዘመን የሰውም ሆነ የእኛ አስተያየት ከፍርድ ለማምለጥ ምክኒያት አይሆኑንም፡፡ ከፍርድ የሚያስመልጠን በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ያመነው ነገር ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ፣ ስለ ዘላለም ሕይወት አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በነገረን እውነት አንጻር የምንዳኝበት የፍርድ ቀን ይመጣል፡፡ ፍርድ የሚሰጠው በዚህ መመዘኛ ብቻ ነው፤ ምክኒያቱም ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፣ የዮሐንስ ወንጌል 12፡48 ‹‹በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል››፡፡ (ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ቅ የተወሰደ) ስለዚህ የዘላለም ሕይወትን አስመልክቶ ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በሌለበት የግሉን አስተያየት ቢሰጠን ልንቃወም ይገባል፡፡ ከነፍሳችን በላይ ምን ሊያሳስበን የሚችል ነገር ይኖራል?
የነፍሳችንን ዋጋ በአለም ያለ ምንም ነገር ሊመጥነው እንደማይችል ያውቃሉ? ማቴዎስ 16፡26 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድነው?›› (ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ቅ የተወሰደ) ነፍሳችን ዘላለማዊ ናት፡፡ እናም ይህችን ነፍስ ለዘላለም በእቶን እሳት ውስጥ እንድትኖር ሊያደርጋት የሚችሉ ጉዳዮችን ሁሉ በቸልታ መመልከት ፈጽሞ አይገባንም፡፡
ክፍል 2 ን በሚቀጥለው ጽሁፌ ይዤልዎት እቀርባለሁ እስከዚያው ቸር እንሰንብት።
ካሱ ቦስተን
Like this:
Like Loading...