ክፍል 6
ኢየሱስ ለደቀ መዝሙርነት ብቁ አይደላችሁም ብሎ የርሱን የደቀ መዝሙርነት መለኪያ ያለፉትናና ወደኋላ የተመለሱትን ጥቂት ሰዎች ባለፉት 5 ክፍል ንባባችን ተመልክተናል በዛሬው ክፍል ንባባችን ደግሞ የመጨረሻውን ተሰናባች ሰው እንመልከት ፦
መሰናበት
“ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ።”
በዚህ ምእራፍ ውስጥ ይህ የመጨረሻው ጠያቂ ነው። የዚህኛው ደግሞ ብዙም ጊዜ የማይወስድና ቤተሰቡን ብቻ ተሰናብቶ ለመምጣት ስለሆነ የሚፈቀድለት ይመስላል። ግን ምን ተባለ? “ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።” አሁንም ኢየሱስ ያየው የሰውየውን ልብ ነው። ኢየሱስን ፊት ለፊት እያየው፣ በሥጋ የተገለጠውን ጌታ እየተመለከተ ልቡ ሙሉ በሙሉ ሳይቀልጥ መቅረቱና፣ ቤተሰቦቹን የሚያስብበት ክፍተት ማግኘቱ ፈጽሞ አለመማረኩን ያሳያል። ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት ውስጥ ማንም ቤተሰቦቹን የተሰናበተ የለም ሁሉም ተሰናብተው ሳይሆን «ትተው» ነው የተከተሉት። ለመሆኑ መተውና መሰናበት ልዩነት አለው እንዴ? አዎ መተው በክርስቶስ ፍቅር ተሸንፎ በዚያው መቅረት ሲሆን መሰናበት ግን በውሳኔ ላይ ቤተሰብ እንዲሳተፍ መፍቀድ ነው። ሊሰናበት ሲሄድ አሳቡን ሊያስቀይሩት መሞከራቸው አይቀርምና።
ጌታን ክርስቶስን ለመከተል ቤተሰብን ይቅርና ሥጋና ደምን (የራስን ማንነት) ማማከር እንኳ አልተፈቀደም። ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ልጁን በርሱ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ከሥጋና ደም ጋር (ከፍጥረታዊ አእምሮውና አስተሳሰቡ) ጋር አልተማከረም። ከርሱ በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩትም አልሄደም። ከሥጋና ከደም ጋርስ አይማከር ከርሱ በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩትስ ለምን አልሄደም? የደቀመዝሙርነት ውሳኔ በማንም ምክርና አስተያየት ተደግፈን የምንወስነው ሳይሆን የራሱ የጠሪው የእግዚአብሔር ዓላማ ገብቶንና የክርስቶስ ፍቅር ነድፎን የምንወስነው ነው። የክርስቶስ ፍቅር ልባችንን ሲነድፈንና የጥሪው ጉልበት ሲነካን ለሌሎች ነገሮች አቅም ያሳጣናል። ደቀመዝሙርነት ኢይሱስን ከመከተል በቀር ሌላ ምንም ነገር ለማድረግ አቅም ማጣት ማለት ነው። የጥሪው ክቡርነትና አጓጊነት ፈጣን ውሳኔን የሚጠይቅ አድርጎታል።
ስለዚህ ለዚህ ሰው ኢየሱስ የመለሰው እንዲህ በማለት ነበር፦ “ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።” (ሉቃ.9:62) እርፍ ማለት ገበሬዎች የሚያርሱበት የእርሻ መሳሪያ ሲሆን ሁለት በሬ ተጠምዶ የሚጎትተውና አራሹ ከኋላ ሆኖ እርፉን በመያዝ ማረሻው መስመሩን ጠብቆ እንዲያርስ የሚጠቀምበት ነው። ጌታ በሚገባው የግብርና ምሳሌ ነው ለዚህ ሰው እየተናገረ ያለው። የተጠመዱት በሬዎች በሙሉ ኃይላቸው ወደፊት እየጎተቱ ባሉበት ሰዓት እርፉን የጨበጠው ገበሬ ወደኋላ ሊመለስ ቢል አይችልም።የበሬዎቹ ጉልበት ወደፊት ይጎትተዋል። ሊመለስ ከወሰነ ግን አንድ ነገር ማድረግ አለበት ይህም እርፉን መልቀቅ ነው።
በዚህ ምሳሌ መሰረት የእግዚአብሔር መንግስት ወደፊት የምትዘረጋና ወደ ፍጻሜ እየችኮለች ያለች መንግስት ናት። ወደ ኋላ የሚመለከቱትን ቆማ ልትጠብቃቸው አትችልም። እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ የሆነውን የመንግስቱን ሐሳብ ለመፈጸም እየተራመደ ነው። የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አሳብ ሁሉም በጊዜው እንዲፈጸም ስለተወሰነ እኛ አንድ ነገር አድርገን እስክንመጣ ድረስ ሊጠብቀን የሚችል አይደለም። የእግዚአብሔር መንግስት ተንቀሳቃሽ መንግስት ናት።በርስዋ ውስጥ ከገባን በኋላ በርስዋ የእንቅስቃሴ ስልት ብቻ ነው ልንንቀሳቀስ የምንችለው። በእግዚአብሔር መንግስት ወስጥ ከገባን በኋላ የራሳችን እንቅስቃሴ ሊኖረን አይችልም። ህይወታችን ሁሉ በርስዋ የእንቅስቃሴ ምህዋር ውስጥ ይመራል።
የእግዚአብሔርን መንግስት የያዝንባትና መንግስቱ እኛን የያዘችበት ዕለት የኛ እንቅስቃሴና ዓላማ ሁሉ ያበቃበት፣ የሞተበት፣ የተቀበረበት ቀን ነው፡፤ እናትና አባትን ለመቅበር የምንፈልግበት ቀን ሳይሆን ራሳችንን ለዚህ ዓለም የምንቀብርበትና በመንግስቱ ውስጥ ትንሳኤን የምናገኝበት ድንቅ ዕለት ነው። መቸም ራሱ የሞተና የተቀበረ ሰው እናት አባቱን ሊሰናበትም ሊቀብርም አይጠይቅም ተቀብሮአልና።
ገበሬው እርፉን ለሚጎትተው የበሬዎች ኃይል መገዛትና እርፉን ጨብጦ እነርሱ ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ብቻ መሄድ እንደሚገባው ሁሉ አንድ ደቀ መዝሙርም የእግዚአብሔርን መንግስት ማለትም ክርስቶስን ካገኘ በኋላ ለመንግስቱ ጉልበት ተሸንፎ መንግስቱ ወደምትሄድበት አቅጣጫ ብቻ የሚሄድ ነው። “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” (ዮሐ.3፡8) ከእግዚአብሔር የተወለደ የመንግስቱ ደቀመዝሙር በነፋስ መመሰሉና ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አለመታወቁ ለምን ይሆን? በራሱ መንገድና መርህ «እናቴንና አባቴን ልቅበር ልሰናበት» በሚለው መርህ መመላለስ አቁሞ በመንግስተ ሰማያት ምህዋር ውስጥ ስለገባ አይደለምን? እናቱንና አባቱን ሊቀብርና ሊሰናበት የሚሄደውንማ ሁሉም ሰው ከየት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ ያውቀዋል የሰው ሁሉ ምልልስ ነውና። ከእግዚአብሔር ተወልደን የክርስቶስን ማንነት ተካፍለን «ከመንፈስ የተወለደ» ስንሆን ግን እንቅስቃሴአችን ሁሉ በእግዛኢብሔር ዙፋን የሚመራ፣ በጉ ወደሚሄድበት ብቻ የሆነ ለሰዎች የማይታይና በሰዎች የማይገመት ይሆናል። ዓለም የሰው ልጆች እንዲመላለሱበት በቀረጸችው የኑሮ መርህ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንግስት ስርዓት እንመላለሳለን። የሂደታችን አቅጣጫ ሰዎች ወደሚሄዱበት አይደለም በጉ ወደሚሄድበት እንጂ። እንደ ነፋስ በዚህ ዓለም እንዳለን ይታወቃል፣ ሰዎች ድምጻችንን ይሰማሉ፣ የእንቅስቃሴአችንን ዱካ ግን ሊያውቁ አይችሉም። እንቅስቃሴአችን በጣም ዝቅተኛ ከሆነው የሰው ልጆች መርህ ወጥቶ በመንግስቱ መንኮራኩር ውስጥ ተሰውሮአልና።
የእንቅስቃሴአችን እዝ ማእከል እግዚአብሔር እንጂ ስጋና ደም፣ የምድር ሥርዓት፣ ፖለቲካ፣ ምድራዊ ጥበብ በጭራሽ አይደለም። ወደ መንግስቱ ስንመጣ የመንግስቱ ጉልበት ዑደት (አዙሪት) ወደርሱ ጎትቶ ካላስገባንና ለዚህ ሰማያዊ ጉልበት ወዲያው ተሸንፈን ኢየሱስን ካልተከተልን የመንግስተ ሰማይ ደቀመዝሙር አይደለንም። ይቀጥላል
ካሱ ቦስተን
እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ ።