የሚያስተራርቁ (የሚታረቁ) ብጹዓን ናቸው !

ከላይ በርዕሴ ላይ እንደምታዩት (በማቲዎስ ወንጌል 5፡9) የተራራው ስብከት ላይ የተገለጹትን ማለትም የብጽዕና መስፈርቶችን መዳሰስ ፈለግሁና ብጹዓን ናቸው ብሎ ጌታ ኢየሱስ የገለጻቸውን ሰዎች ማንነት ውስጥ እራሳችንን እንድንፈትሽና እንድናይ አንዷን አውጥቼ እንድናያት ፈለግሁ። 

      የጌታ ደቀመዝሙር ሰዎችን ለማስታረቅና ሰላምን ለመፍጠር የተጠራ አገልጋይ ነው። ጌታ ኢየሱስ ሰዎችን ከእግዚአብሄር ጋር፤ ሰዎችን ከሰዎች ጋር እና ሰዎችን ከራሳቸው ጋር በማስታረቅ ሰላም የሚያደርጉትን፤ እነዚህን የእግዚአብሄር ልጆች ይባላሉ ብሎ ገልጾአቸዋል። ስለዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን ይህንን ተግባር ለማድረግ መጣር አለብን እላለሁ። ዛሬ ዛሬ እንደምናየውና እንደምንመለከተው ግን በምንኖርበት አካባቢ ከእግዚአብሄርና ከሰዎች ጋር ሰላም አጥተን የምንኖር ብዙዎች ነን። የተጠራነው እርቅ እንድንፈጥርና ሰላምን እንድናወርድ ነው። የብጽዕና ህይወት መገለጫችን ሰላምንና እርቅን መፍጠራችን ነውና። አለበለዚያ የተባለው ተቃራኒ (የእግዚአብሄር ልጆች) አይባሉም ይሆናል። 

   አሁን እየታየ ያለውን የደቀመዛሙርትነት ህይወታችንን ስንመረምረው ግን፤ ለሰላምና ለእርቅ የተጠራን፤ እርስ በርሳችን ተከፋፍተንና ተከፋፍለን ለእርቅና ለግልግል ማስቸገራችንን ላየ ትዝብት ውስጥ ሳይከተን አይቀርም እላለሁ።  ዓለምን ከእግዚአብሄር ጋር ለማስታረቅ የተጠራች ቤተክርስቲያን፤ እርስ በርስ ተጣልታ እንድታስታርቀው በተላከችበት ዓለም፤ በተቃራኒው ለእርቅ ግልግል ውስጥ መግባቷ፤ ብጽዕናዋን እንዳታገኝ ያደርጋታል። ከብዙ ትግል በኋላ እንኳን የመታረቅ ሂደት ውስጥ ስትገባም  “እታረቃለሁ፤ ግን እንደድሮው አልሆንም” በማለት የታረቁ የሚመስሉ ግን ያልታረቁ ቤተክርስቲያን(ክርስቲያኖች)፤ አማንያን ወይም ደቀመዛሙርት መሆናችንን እንደውም ድንበርና ደንብ መተዳደሪያ አበጅተን የተቀመጥን እንዳለን ቤቱ ይቁጠረው።

   ዛሬም እንደፈርኦን ልባችንን አደንድነን በመቀመጣችን፤ የምድር ሁሉ ቀውስ ውስጥ መግባት ወይም አለመቆም ምክኒያት ሆነን ቢሆንስ ? እላለሁ ።     ጆሮ ያለው ይስማ !!    

ተባረኩልኝ።  

ካሱ ቦስተን 

linkedin.com/in/kassuboston

https://www.instagram.com/kasselsa97

https://www.facebook.com/kasselsa97

  ቅዱሳን ሁኑ !

 ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት1:15-16

​(ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:20-23)

ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም። በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡

     እግዚአብሄር እኔ በአህዛብ ፊት እናንተን ከነርሱ ውጡና የተለያችሁ ሁኑ እርኩሱንም ነገር አትንኩ ብያችሁ ነበር ነገር ግን እናንተ በመሃከላቸው ሆናችሁ ቅዱሱን ስሜን አረከሳችሁት: ስለዚህ እኔ እንደሎጥ እራራላችሁና እጃችሁን ይዤ አወጣችኋለሁ ለራሴ ለቅዱሱ ስሜ ስል እቀድሳችኋለሁ: ያኔ እናንተን ስቀድስ መልካም አድርጌ ስሠራችሁና በናንተ ውስጥ ስኖር አህዛብ እኔ እግዚአብሄር እንደሆንኩ ያውቃሉ እኔ እራሴ ስሜን አስከብራለሁ እናንተን እቀድሳለሁ እንደገናም በእናንተ እቀደሳለሁ ይላል ይህን የማደርገው ግን እናንተ ስለሰራችሁት ስለመልካም ስራችሁ ሳይሆን ስለራሴ ቅዱስ ስለሆነው ስሜ ነው ይላል ምክኒያቱም እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን እንድትሆኑ ስለምፈልግና እኔንም ማየት የምትችሉት በቅድስና ስትኖሩ ስለሆነ ነው፡፡

   እንግዲህ መንፈሳዊ ቤት ሆናችሁ እንድትሰሩና እኔ እንድኖርባችሁ ይህን ከዚህ የሚቀጥለውን በመካከላችሁ አደርጋለሁ ይላል እግዚአብሄር፡፡

     ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ፥ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፥ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። (ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:24-28) አሜን አሜን አሜን!!!

kasselsa97

https://youtu.be/LbCx7WVy3ZY

https://www.tiktok.com/@kassuboston

linkedin.com/in/kassuboston