የሚያስተራርቁ (የሚታረቁ) ብጹዓን ናቸው !

ከላይ በርዕሴ ላይ እንደምታዩት (በማቲዎስ ወንጌል 5፡9) የተራራው ስብከት ላይ የተገለጹትን ማለትም የብጽዕና መስፈርቶችን መዳሰስ ፈለግሁና ብጹዓን ናቸው ብሎ ጌታ ኢየሱስ የገለጻቸውን ሰዎች ማንነት ውስጥ እራሳችንን እንድንፈትሽና እንድናይ አንዷን አውጥቼ እንድናያት ፈለግሁ። 

      የጌታ ደቀመዝሙር ሰዎችን ለማስታረቅና ሰላምን ለመፍጠር የተጠራ አገልጋይ ነው። ጌታ ኢየሱስ ሰዎችን ከእግዚአብሄር ጋር፤ ሰዎችን ከሰዎች ጋር እና ሰዎችን ከራሳቸው ጋር በማስታረቅ ሰላም የሚያደርጉትን፤ እነዚህን የእግዚአብሄር ልጆች ይባላሉ ብሎ ገልጾአቸዋል። ስለዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን ይህንን ተግባር ለማድረግ መጣር አለብን እላለሁ። ዛሬ ዛሬ እንደምናየውና እንደምንመለከተው ግን በምንኖርበት አካባቢ ከእግዚአብሄርና ከሰዎች ጋር ሰላም አጥተን የምንኖር ብዙዎች ነን። የተጠራነው እርቅ እንድንፈጥርና ሰላምን እንድናወርድ ነው። የብጽዕና ህይወት መገለጫችን ሰላምንና እርቅን መፍጠራችን ነውና። አለበለዚያ የተባለው ተቃራኒ (የእግዚአብሄር ልጆች) አይባሉም ይሆናል። 

   አሁን እየታየ ያለውን የደቀመዛሙርትነት ህይወታችንን ስንመረምረው ግን፤ ለሰላምና ለእርቅ የተጠራን፤ እርስ በርሳችን ተከፋፍተንና ተከፋፍለን ለእርቅና ለግልግል ማስቸገራችንን ላየ ትዝብት ውስጥ ሳይከተን አይቀርም እላለሁ።  ዓለምን ከእግዚአብሄር ጋር ለማስታረቅ የተጠራች ቤተክርስቲያን፤ እርስ በርስ ተጣልታ እንድታስታርቀው በተላከችበት ዓለም፤ በተቃራኒው ለእርቅ ግልግል ውስጥ መግባቷ፤ ብጽዕናዋን እንዳታገኝ ያደርጋታል። ከብዙ ትግል በኋላ እንኳን የመታረቅ ሂደት ውስጥ ስትገባም  “እታረቃለሁ፤ ግን እንደድሮው አልሆንም” በማለት የታረቁ የሚመስሉ ግን ያልታረቁ ቤተክርስቲያን(ክርስቲያኖች)፤ አማንያን ወይም ደቀመዛሙርት መሆናችንን እንደውም ድንበርና ደንብ መተዳደሪያ አበጅተን የተቀመጥን እንዳለን ቤቱ ይቁጠረው።

   ዛሬም እንደፈርኦን ልባችንን አደንድነን በመቀመጣችን፤ የምድር ሁሉ ቀውስ ውስጥ መግባት ወይም አለመቆም ምክኒያት ሆነን ቢሆንስ ? እላለሁ ።     ጆሮ ያለው ይስማ !!    

ተባረኩልኝ።  

ካሱ ቦስተን 

linkedin.com/in/kassuboston

https://www.instagram.com/kasselsa97

https://www.facebook.com/kasselsa97

Leave a comment