የማቴዎስ ወንጌል 6፡33 ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
“የእግዚአብሔር መንግሥት ምንድን ነው?” የእግዚአብሔር መንግሥት የኢየሱስ ትምህርት ዋና ትኩረት ነበር። በመንፈሳዊነት ለማደግ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መረዳት አለብን። የእግዚአብሔር መንግሥት መንፈሳዊ መንግሥት እንጂ በአሁኑ ዘመን ያለ ሥጋዊ መንግሥት አይደለም። ሆኖም፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለማችን ውስጥ አለ እና በብዙ መንገዶች ተጽዕኖ ያሳድራል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ መንግሥት መሪ ወይም ንጉሥ አለው። የእግዚአብሔር መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ዮሐንስ 3፡3 ኢየሱስም መልሶ፡— እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡ አለው።
ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት እና ለመግባት ዳግመኛ መወለድ ወይም መዳን አለበት። የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች በኢየሱስ ብቻ ያመኑ ናቸው።
ዳንኤል 2:44፣ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፥ መንግሥቱም ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃቸዋል ወደ ፍጻሜአቸውም ያደርሳቸዋል ለዘላለምም ጸንቶ ይኖራል።
ነቢዩ ዳንኤል የእግዚአብሔር መንግሥት የማይፈርስ ዘላለማዊ መንግሥት እንደሆነ ነግሮናል። መንግሥተ ሰማያት ሌላውን መንግሥት ያደቃል እና ያጠፋቸዋል። የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚቃወመው መንፈሳዊ መንግሥት የሰይጣን መንግሥት ነው። የሰይጣን መንግሥት ዜጎች የማያምኑ ናቸው። የሰይጣን መንግሥት በዓለም ሥጋዊ መንግሥታት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። ኢየሱስ እንድንጸልይ አስተምሮናል…
ማቴዎስ 6:10፣ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።
የእግዚአብሔር መንግሥት በሰማይ ትገዛለች፣ በዚያ ምንም የሚወዳደሩ መንግሥታት የሉም። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንደሆነው ፍጹም በሆነ መልኩ ተፈጽሟል። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደዚህ ምድር እንድትመጣ በየዕለቱ መጸለይ አለብን። እናም የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንደሆነው ሁሉ እዚህም በምድር እንዲሆን መጸለይ አለብን።
የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መንግሥቱ የምታድግበት ዋና መንገድ ናት። የእግዚአብሔር መንግሥት የሚያድገው ሰዎችን ከሰይጣን መንግሥት በማዳን ነው። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ስናድን መንግሥቱን እናሰፋዋለን። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ ከዋና ዋና መንገዶች አንዱን አስተምሮናል።
የሉቃስ ወንጌል 10፡9 በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው።
የታመሙትን ለመፈወስ የእግዚአብሔርን ኃይል ስናመጣ፣ መንግሥቱ ትቃረባለች። ሰዎች በኃጢአታቸው ተፈርዶባቸዋል፣ ንስሐ ገብተው ወንጌልን ሰምተው ኢየሱስን ሲቀበሉ ግን የእግዚአብሄር መንግስት እየጽፋፋች ትመጣለች። ዛሬ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ከኢየሱስ የበለጠ እንማራለን።
የእግዚአብሔር መንግሥት እንዴት ያድጋል?
የሉቃስ ወንጌል 13፡18 እርሱም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ?
በወንጌሎች ውስጥ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ምን እንደሚመስል ብዙ ታሪኮችን ወይም ምሳሌዎችን ሰጥቷል። የእግዚአብሔር መንግሥት እግዚአብሔር የሚገዛበት፣ ፈቃዱ የተደረገበት ግዛት ነው። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሚናገራቸው ታሪኮች ብዙውን ጊዜ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተሳሳተ አስተሳሰብን ለማስተካከል ነው። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ በማስተማር ብዙ ጊዜ አሳልፏል ምክንያቱም ይህ መንግሥት በጣም አስፈላጊ ነበር። ሆኖም ስለ መንግሥቱ ያስተማረው ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ ችላ ተብለዋል፤ አሁንም ችላ እየተባለ ነው።
የሉቃስ ወንጌል 13፡19 ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ።
የሰናፍጭ ዘር ልክ እንደ አሸዋ ቅንጣት የሚያክል ከትንንሽ ዘሮች አንዱ ነው። ሆኖም ዘሩ ሲያበቅል እና ሲያድግ የሰናፍጭ ተክል ወይም ዛፉ እስከ ዘጠኝ ጫማ ቁመት ሊደርስ ይችላል። በቅርንጫፎቹ ውስጥ ወፎች ጎጆአቸውን ለመሥራት በቂ ነው። የኢየሱስ ነጥብ ምንድን ነው?
ሰዎች ቃሉን መናገርና መመስከርን ለተናገሩት ሰውም መጸለይን በጣም ትንሽ ነገር አድርገው ይቆጥራሉ። የሰናፍጭ ዘር ባልዳነ ሰው ላይ የምሥክርነት ቃል ወይም ጸሎቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የሰናፍጭ ዘር ለጌታ ቤተክርስቲያን የምትሰጡት አስራት ሊሆን ይችላል። በኢየሱስ ስም የሚደረገው ማንኛውም ነገር እንደ የሰናፍጭ ቅንጣት ይመስላል እና ብዙ ጊዜ በጣም ትንሽ ይመስላል። ነገር ግን፣ ኢየሱስ በጣም እንደሚያድግ እና ለብዙዎች በረከት እንደሚያመጣ ተናግሯል።
ሉቃስ 13:20—21፣ ደግሞም፡— የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስለዋለሁ? አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉም እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ።
ይህንን ታሪክ ለመረዳት ሶስት መለኪያ ዱቄት ወደ 50 ፓውንድ ዱቄት በጣም ትልቅ መለያ መሆኑን ማወቅ አለብን፤ ሴትየዋ በዱቄት ውስጥ የቀላቀለችው እርሾ በጣም ትንሽ ነበር፤ ሆኖም እርሾው ሙሉውን የዱቄት መጠን በማቡካት ዳቦ አመጣ። ይህ ታሪክ የሚያሳየን ምንም እንኳን መንግሥቱ ትንሽ ቢመስልም በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል። የእግዚአብሔር መንግሥት ከትንሽ ወደ ትልቅ ያድጋል።
በ1906 በአዙሳ ጎዳና የነበረው ታላቅ መነቃቃት የጀመረው በአንድ “ፍራንክ ባርትልማን” በተባለ ግለሰብ ነው። ይህ ሰው መነቃቃት ወደ ሎስ አንጀለስ እንዲመጣ ሲማልድ ነበር። ከዊልያም ሴይሞር ጋር የተደረገው የመጀመሪያው ስብሰባ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲወድቅ ከ8 ሰዎች ጋር ብቻ ነበር። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ድነዋል፣ ተፈውሰዋል። እናም እጅግ በጣም ለማመን በሚከብድ ከተፈጥሮ በላይ በሆነ መንገድ ስዎች ሲድኑና የእግዚአብሄር መንግስት ሲሰፋ ታይቷል። የዚያ ትንሽ ጅምር ተጽእኖ በዓለም ዙሪያ በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁ አማኞች በሁሉም የአለም ሀገራት ተሰራጭተዋል።
ስለ መንግሥቱ እድገት ወደ እግዚአብሔር የምትጠራውን የአንድ ሰው ወይም የጥቂት ቡድን ወይም የአንድ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሥልጣን ትንሽ አድረገህ አትመልከት። እነዚህ የኢየሱስ አጫጭር ታሪኮች እርስዎን ባሉበት ቦታ እምነትን ወደ ልብዎ ያምጣ። የእግዚአብሔር ስጦታ ልክ እንደ ትንሽ የሰናፍጭ ቅንጣት ወይም ትንሽ እርሾ እንደሆነ ይሰማሃል? ስጦታህን ለእግዚአብሔር ስታቀርብ እርሱ ብዙዎችን ለመባረክ እንደሚያበዛው እመን።
ወደ እግዚአብሄር መንግስት መግቢያው እንዴት ነው ?
ሉቃስ 13:23—24፣ አንድ ሰውም፦ ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦
በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም።
ኢየሱስ “የሚድኑት ጥቂቶች ናቸውን ?” የሚለውን ጥያቄ አልመለሰም። በዚህ ምንባብ ውስጥ እርሱ ግን በማቴዎስ 7፡13 ላይ ያለውን ተመሳሳይ ጥያቄ ነው የመለሰው።
ማቴዎስ 7፡13-14 “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
ስለዚህ፤ አዎ ከማይድኑት ጋር ሲነጻጸር፣፤ የዳኑት ጥቂቶች ይሆናሉ። ኢየሱስ እዚህ ጋር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት መንገዱ በጠባብ በር እንደሆነ ነግሮናል። በጠባቡ በር ለመግባት መጣር እንዳለብን ይነግረናል። መጣር የሚለው የግሪክ ቃል መታገል፣ በአትሌቲክስ ውድድር መሳተፍ ወይም መታገል ማለት ነው። ከታዋቂ እምነት በተቃራኒ ወደ ጠባብ በር ለመግባት እና ለመዳን ቀላል አይደለም። እንዲያውም፤ ብዙዎች ወደ ጠባቡ በር ለመግባት እንደሚሞክሩ፣ ነገር ግን እንደማያልፉት እና እንደማይገቡበት ኢየሱስ ነግሮናል።
ሉቃስ 13:25፣ ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ልታንኳኩ ትጀምራላችሁ እርሱም መልሶ፦ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላችኋል።
በዚህ ታሪክ ውስጥ ጠባብ በር ያለው ቤት፤ የቤቱ ጌታ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ዳግም ሲመለስ ወይም ኢየሱስን ያላመነ ሰው ሲሞት፤ ያን ጊዜ ኢየሱስ ማን እንደሆነ ያውቃል። ልክ እንደዚያው ጠባብ በር ያለውን ቤት በር እያንኳኩ ለመግባት ይሞክራሉ፤ ነገር ግን በሩ በቋሚነት ከውስጥ ተዘግቷል። ኢየሱስ ከቤት ውስጥ ሆኖ መልስ ይሰጣል፤ ከወዴት እንደሆናችሁ አላውቃችሁም ይላል።
ሉቃስ 13:27—28፣ እርሱም፦ እላችኋለሁ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ይላችኋል።
አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ኢየሱስ በዚህ በምድር ህይወት በእርሱ ያላመኑትን ሰዎች እንደማያውቅ ደጋግሞ ተናግሯል። ክፉ አድራጊዎችም ይላቸዋል። የልቅሶ እና ጥርስ ማፋጨት ቦታ ውስጥ እንዳሉ በዘላለም ስቃይ ውስጥ እንደሚጣሉና ወደ ገሃነም እንደተላኩ ይናገራል።
በኢየሱስ ዘመን እርሱን እንደ መሲህ ያልተቀበሉትን ሃይማኖተኛ አይሁዳውያንን እያነጋገረ ነበር። ሉቃስ 13:29—30፣ ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፥ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፥ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።
ኢየሱስ የሚናገረው በኢየሱስ የሚያምኑትን አሕዛብ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንደሚሆኑ ነው። በዚህ ዓለም የመጨረሻ የሚመስሉ ሰዎች፣ ማዕረግ ወይም ሀብት የሌላቸው፣ በመንግሥቱ የመጀመሪያ ይሆናሉ። ሌሎች በዚህ ዓለም የመጀመሪያ የሚመስሉ፣ በሥልጣንም ሆነ በሀብት የመጀመሪያ መሳዮች የመጨረሻ ይሆናሉ ይላል። በጠባቡ በር በመታገል ወደ መንግስቱ ይገባሉ።
ቤተክርስቲያን ዛሬ ራሴን ጨምሮ አማኝ ለመሆን የወሰንንባትን እና ያቻልንበትን ያችን ቅጽበታዊ ጸሎት በጣም ቀላል እናደርጋታለን። በአንድ በኩል ቀላል ነው፣ ንስሀ መግባት እና በኢየሱስ ማመን ወደመንግስቱ ያስገባናል። ሆኖም፣ ብዙ ሰዎች ያንን ቀላል ጸሎት ይጸልያሉ ነገር ግን ህይወታቸውን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ አይሰጡም አያስገዙምም። ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ለመጀመር በጣም ይታገላሉ።
በህይወት ውስጥ አቧራማ በሆነ መንገድ ላይ ስለሚሄድ መንገደኛ ለአንድ ደቂቃ ያህል እናስብ። ትልቅ ቦርሳ አለው፤ ሌሎች ነገሮችን ደግሞ በቀበቶው እና በእጁ ይዞ እየተጓዘ ነው፤ ወደ ውብ የእግዚአብሔር መንግሥት ቤት ሲቃረብ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚልብእጣም ደስ ይላል፤ እዚያ ገብቼ መደሰትና ማረፍ እፈልጋለሁ ብሎም ወደበሩ ቀረበ። በውስጡ በጣም የሚያስደስቱ እና የሚማርኩ ነገሮችን ተመለከተ። ነገር ግን በበሩ ውስጥ ለመግባት ሲሞክር በጣም ጠባብ መሆኑን ተገነዘበ፤ የቻለውን ያህል ሞክረ በተሸከመው ነገር ሁሉ በሩን ማለፍ አልቻለም። ይህ ግለሰብ የተሸከማቸው ነገሮች፤ ንብረቶቹ ገንዘቡን፣ ግንኙነቶቹን፣ ስራውን፣ ግቦቹን እና ኃጢአቶቹን ይወክላሉ።
ሰውዬው አንዳንድ ነገሮችን ያስቀምጣል፤ ነገር ግን አሁንም በበሩ ውስጥ መግባት አልቻለም። በመጨረሻም በጠባቡ በር ለመግባት ያለውን ሁሉ መተው እንዳለበት ይገነዘባል። በሚያሳዝን ሁኔታ ንብረቶቹን እንደተሸከመ መግባት ስላልቻለ መንገዱን ይቀጥላል። በጠባቡ በር ለመግባት ሁሉንም ነገር አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለምና።
ሆኖም ይህ ሰው አንዳንድ ነገሮችን አስቀምጧል፤ አልፎ ተርፎም አልፎ አልፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዷልና አማኝ እንደሆነ ያስባል። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ አይደለም። ጠባቡን በር አላለፈውም። ወደ ጠባብ የመንግስቱ በር ለመግባት ሁሉንም ነገር ማስቀመጥ ይጠይቃል።
ከእግዚአብሔር መንግሥት የተገለለው ማን ነው?
ሉቃስ 13:32፣ እንዲህም አላቸው፦ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ፦ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት።
ኢየሱስ ንጉሥ ሄሮድስን ያልጨነቀው ቀበሮ መሆኑን እየተናገረ ነው። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ተልእኮ የመንግስቱ ስራ ላይ ነበር። አጋንንትን በማባረር እና ሰዎችን በመፈወስ የ እግዚአብሄርን መንግስትን ኃይል ማሳያዎች ወይም ምልክቶች እንደሆኑ ጠቅሷል። ኢየሱስ ለኃጢአታችን ሊሞት ወደ መስቀል እያመራ መሆኑን እና ጊዜው እንደቀረበ ያውቅ ነበር።
ሉቃስ 13:34 ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም።
እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ነበረች። ሆኖም ባለፉት መቶ ዘመናት ውስጥ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢያት ተገድለዋል እና ተወግረው ነበር። ኢየሱስ ሁሉም የአይሁድ ህዝቦች እንደ መሲህ እንዲያምኑት ፈልጎ ነበር። ሆኖም፣ ንስሐ ለመግባት እና በኢየሱስ ለማመን ፈቃደኛ አልነበሩም። ስለዚህ፣ ባለማመናቸው የተነሳ፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት ይገለላሉ ማለት ነው። ኢየሱስ በማያምኑት እስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ተናገረ።
ሉቃስ 13:35፣ እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።
በታሪክ እንዳየነው ኢየሱስ ወደ አባቱ ካረገ ከ40 ዓመታት በኋላ፣ በ70 ዓ.ም.፣ ሮማውያን ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ በሙሉ እንዳፈረሱት እናውቃለን። በኢየሱስ ዘመን እና በታሪክ ውስጥ፣ አብዛኞቹ አይሁዶች ኢየሱስን መሲህ እንደሆነ አላወቁም እና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አልገቡም ነበር። አንድ ቀን፣ ኢየሱስ ተመልሶ ይመጣል እናም ሁሉም አይሁዳዊም ጨምሮ ያዩታል። እርሱ ከመመለሱ በፊት በእርሱ የሚታመኑት ብቻ ይድናሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም ይገባሉ። በኢየሱስ ያላመኑት ከእግዚአብሔር መንግሥት የተገለሉ ናቸው።
ከእግዚአብሔር መንግሥት የተገለሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጨለማ ግዛት ተብሎ በተጠራው በሰይጣን መንግሥት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ። ከገሃነም ማምለጥ የለም፤ በሲኦል ውስጥ የእግዚአብሔር መገኘት የለም፤ እንዲያውም፣ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ውስጥ በገሃነም ውስጥ ያሉት ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት መመልከት እንደሚችሉ፣ ይህም ስቃዩ እንዲጨምርባቸው ያደርጋል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ክፍል መምረጥ በህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊው ውሳኔ ነው።
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብቸኛው መንገድ ንስሐ መግባት እና በኢየሱስ ማመን ነው። ሁሉንም ነገር አስቀምጠህ በጠባቡ የመንግሥቱ በር መግባቱን ምረጥ። አንድ ሰው ኢየሱስን የማያውቅ ከሆነ፣ የመንግስቱ አካል አይደለም እና አልዳነም።
የእግዚአብሔርን መንግስት መረዳት በህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት የኢየሱስ ትምህርት ዋና ነጥብ የሆነውም ለዚህ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ዘር ስንዘራ የእግዚአብሔር መንግሥት በዙሪያችን እያደገ ነው። ምንም እንኳን በሰዎች ህይወት ውስጥ በትንሹ ቢጀምርም፤ በትናንሽ ቡድኖች፤ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ከተማዎች፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ያድጋል።
የመንግስቱ አካል ለመሆን በጠባቡ በር ለመግባት መታገል አለብህ። ያንንአልፎ ለመግባት ሁሉም ሰው ያለውን የተሸከመውን ሁሉ ማስቀመጥ አለበት። ሁሉንም ለኢየሱስ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ከመንግሥቱ ውጭ ይሆናሉ።
ስለዚህ ይህንን መልእክት እያነበቡ እና ከመንግስቱ ውጭ መሆንዎትን እያወቁ ከሆነ እባክዎ ዛሬውኑ ወደዚህ መንግስት ለመግባት ይወስኑ። ወደመንግስቱ ለመግባት እና የዘላለምን ህይወት ለማግኘት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው መንገድ ደግሞ፤ እርስዎን ለማዳን ስለሃጢያትዎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞት፤ በመቀበር፤ በሶስተኛውም ቀን ከሞት በመነሳት፤ ወደመጣበት ወደ አብ መንግስት በማረግ፤ ደግሞ በክብር እመለሳለሁ እንዳለ፤ ዳግመኛ የሚመለሰውን ጌታ ኢየሱስን የህይወትዎ ጌታ እና አዳኝ አድርገው በመቀበልና፤ በእርሱ ጸንተው በመኖር ነውና ይህንን ያድርጉ። ጌታም ይረዳዎታል።
ጆሮ ያለው ይስማ !
ይህ የመጨረሻው ደውል የተሰኘው ድህረ ገጽ የማንቂያ ደውል እንደሆነም ያስቡ !
ካሱ ቦስተን
ይህንን ጽሁፍ ወደውት ከሆነ ላይክ በማድረግ እንዲሁም ድህረ ገጹን ሰብስክራይብ ቢያደርጉ ሌሎች ጽሁፎች ሲለቀቁ ወዲያው እንዲደርስዎት ይሆናል። ለሌሎች በማካፈልም የድርሻዎትን ይወጡ።
እንዲሁም ከታች ባሉት ሌሎች ዌብሳይቶች ላይ ያገኙኛል ሊንኩን በመጫን ይፈልጉኝ አመሰግናለሁ።
https://www.tiktok.com/@kassuboston
https://www.instagram.com/kasselsa97
