(የዮሐንስ ወንጌል 10:11) መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል
(የዮሐንስ ወንጌል 10:14-15) መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። (የሃዋርያት ሥራ 20፡28)
እረኛ (የመጽሃፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 178) በጎችና ፍየሎችን ከብቶችንም የሚያሰማራ፤ የጠፋውን የሚፈልግ፤ ከአውሬዎች የሚጠብቅ በማለት ይፈታዋል።
እረኛ ሕይወት ባለው መንጋ ላይ የሚሾም ነው፡፡
እረኝነት በሁለት መንገድ ይታያል፦ አንዱ ቅጥር ሲሆን ሁለተኛው ሹመት ነው፡፡ (ቅጥር ህዝቡ ያስፈልገኛል ይሾምልኝ (ይቀጠርልኝ) ብሎ ልክ የእስራኤል ህዝብ ንጉስ ያስፈልገናል አንግስልን ብለው ሳሙኤልን እንዳስጨነቁና ሳኦል እንደነገሰላቸው ያለ አይነት ማለት ነው)። ሹመት ግን እግዚአብሄር ለህዝቡ ወይም በህዝቡ ላይ እረኛ ሲሾም (ይህ ግን በእግዚአብሄር ጥሪና በእግዚአብሄር ምሪት ለሚያስፈልገው ህዝብ እግዚአብሄር ሲሾም ነው)።
ሕይወት ያለው ነገር ተጠሪ ወይም እረኛ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ዓለም ሲዋቀር መሪና ተጠሪ ያለበት ዓለም ነው፡፡ ስለዚህ ሦስት ታላላቅ ተቋማት እረኛ ወይም መሪ አላቸው፡፡ ለቤተሰብ አባወራ፣ ለአገር ንጉሥ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ እረኛው ናቸው፡፡ በዚህ አገላለጽ እረኛ ወይም መሪ ወደ መልካም ግብ የሚወስድ ንጉስ ወይም አባወራ ማለት ነው፡፡
በእስራኤል አገር እረኛ ከፊት ለፊት ድምፁን እያሰማ የሚሄድ ሲሆን፤ በጐቹ የእረኛቸውን ድምጽ እየሰሙ ይከተሉታል፡፡ እረኛ ሁሌም ከፊት የሚቀድም ነው፡፡ እረኛው ሲቀድም መሪ ይሆናል፡፡ ከኋላ ከሆነ ነጂ ይሆናል፡፡ እረኛው ሲቀድም በዜማ መንጋውን ያስከትላል፡፡ ከኋላ ሲቀር ደግሞ በጅራፍና በዛቻ በማስፈራራት ይነዳል። የአገራችን እረኝነት መንጋው ከፊት እረኛው ከኋላ ነው፡፡ ይህ በብዙ የሕይወት መስክ ያለ ነባራዊ ችግራችን ይመስላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ አይመሩም፤ ሣንቲም የሚጥለው ሕዝብ ይመራል፡፡
እብራውያኖች ደግሞ መንጋዎቻቸውን በሰለጠነ ውሻ ያስጠብቁ ነበር። ለምስክር ይሆን ዘንድ ኢዮብ የነበሩትን ከብቶች በውሻ ያስጠብቅ እንደነበር መጽሃፍ ቅዱሳችን ያስረዳናል። (ኢዮብ 30፡1) እነዚህ ውሾች መንጋዎችን ወደ ለመለመ መስክ አይወስዱም፤ እረፍት ወደአለበት ውሃ ዘንድ አይመሩም፤ መንጎቹ ተሰብስበው ባሉበት ስፍራ መጠበቅ ይችሉ ይሆናል፤ ከመንጎቹም መሃከል ወጣ ለማለት የምትፈልገዋን እንስሳ በጩኸት ወይም በመናከስ ሊመልሷት ይችሉ ይሆናል። እረኛ የሚያስብል አንዳችም ባህሪ ኝ የላቸውም።
መልካም እረኛ የእርሱ ያልሆነውን መንጋ በአደራ ተቀብሎ ከራሱ በላይ ይንከባከባቸዋል፡፡ መልካም እረኛ የሚያሲዘው ነገር ስለሌለ የገዛ ነፍሱን አስይዞ እረኛ ይሆናል፡፡ መልካም እረኛ ራሱን ካልሰጠ እረኛ አይሆንም፡፡ መልካም የተባለ እረኛ እንዳለ ሁሉ መልካም ያልተባለ እረኛም አለ።
መልካም እረኛ፡–
1- የእኔ የሚላቸውን ነገሮች አስቀምጦ ይጀምራል፡– መልካም እረኛ ሀብቱን፣ ሥልጣኑን፣ እውቀቱን፣ የኔ የሚላቸውን እንዲሁም እኔነቱን አስቀምጦ መጀመር አለበት፡፡ ራሱን የሰጠ፤ የኔ የሚለው አንዳችም ነገር የሌለው መሆን አለበት፡፡ ራሱን የሰጠ በሌላ አይታማምና፡፡
2- ዘመኑን ይሰጣል፡- መልካም እረኛ ቀን ከመንጋው ጋር ይውላል፡፡ መንጋው ቀኑን በሙሉ ይበላል እርሱ ግን ጦሙን ሊውል ይችላል፡፡ ማታም በበረቱ ውስጥ ቆጥ ላይ ያርፋል፡፡ እረኛ ማለት ለቅጽበት ከመንጋው የማይለይ ነው፡፡ ስለዚህ እረኛ ዘመኑን ለመንጋው የሰጠ ነው፡፡ እንዲሁም እረኛ የዘመኑን ሽራፊ፣ የጊዜውን ጭላጭ ሳይሆን የዕድሜውን አስኳል ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ እረኛ እንደ ኮንትራት ሠራተኛ፣ የሚሻውን ሲያገኝ የሚታጠፍ አይደለም፡፡ እረኝነት ቀን መግፊያ፣ የሚፈልጉትን ጉዳይ መጠበቂያ አይደለም፡፡ እረኛ አገልግሎቱ ለተፈጠረበት ዓላማ የሚጓዝበት ግብ ያለው ነው፡፡ እረኛ መላ ዘመኑን መስጠት፣ ከመንጋው ጋርም ያለ ማቋረጥ መገናኘት አለበት፡፡
3- ከአራዊት ይናጠቃል፡- እረኛ የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ መንጋውን ከአውሬ ያስጥላል፡፡ እንዲሁም ከአጋንንት፣ ከዓለም ምእመናንን መታደግ የተሰጠው የስራ ድርሻው ነው፡፡ ከአውሬ ሲያስጥል መቊሰሉ አይቀርም፡፡ ከእሳት ሲያወጣ መለብለቡ አይቀርም፡፡ በዚህ ጊዜ በጐቹ የተከፈለላቸውን ዋጋ አያውቁትም፣ ላያመሰግኑትም ይችላሉ፡፡ እረኛው ግን ለመንጋው ሲል ይህን ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡ አዎ እረኛ ለመሆን ራስን መስጠት ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም መያዣው ነፍስ ነው፣ ዳግመኛም ዘመንን መስጠት ይጠይቃል፣ ከአራዊት ጋር መታገልም ያስፈልገዋል፡፡ መልካም እረኛ የሆነ ራሱን መስጠት ካልቻለ መንጋውን ለመጠበቅም ሆነ ለመመገብ አይችልም፡፡ የእረኝነት ቊልፉ ራስን መስጠት ነውና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እረኛ በሆነ ጊዜ የፈረመው በደሙ ነው፡፡ የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ፡- “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ….” ይላል (13÷20)፡፡
ጌታችን የሕይወታችን ብቻ ሳይሆን የአገልግሎታችንም አርአያችን (ሞዴላችን) ነው፡፡ ጌታችን የልደቱን ምሥጢር ለካህናት ሳይሆን ለእረኞች መግለጡ የእረኞች አለቃነቱን ይሣያል፡፡ በዘመናትም ታላላቅ ምሥጢራት የተገለጡት ለእረኞች ነው፡፡ ያዕቆብ፣ ዳዊት እረኞች ነበሩ፡፡ ዳዊትን ስንመለከት የሚጠብቃቸውን በጎች ለራሱ ነፍስ ሳይሳሳ ከአውሬ አፍ መንጭቆ የሚያወጣ ነበር።
በሌላ መልኩ የበጎችን በረት የሚጠብቅ (ሌላ እረኛ መሳይ) የተቀጠረ፤ በር ላይ የሚቆም፤ ጠባቂ ብቻ የሆነ በበረቱ ውስት ያሉት በጎች ሁሉ የራሱ ያልሆነ፤ ለበጎቹ ግድ የሌለው፤ ደግሞ ጠባቂ ወይም ተቀጣሪ የሚባል መልካም ያልሆነ እረኛ፤ በጎቹን ሊተናኮል የሚመጣ አውሬ ቢመጣ ትቶ የሚሸሽ አይነት፤ ህይወቱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ሊሰጥ የማይችል አይነት፤ ተቀጣሪ ወይም በር ላይ ብቻ ሆኖ የሚጠብቅ ጠባቂ እረኛ አለ።
ሃዋርያው ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን መሪዎች መመሪያ ሲሰጥ መልካም መሪዎች ማለትም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኞች ሆነው በክርስቶስ የተዋጀውን ህዝብ ይጠብቁ ዘንድ፤ የርሱን አርዓያ ይከተሉ ዘንድ አዟል። እንዲህ በማለት ” በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። (የሃዋርያት ሥራ 20፡28)” መልካም እረኝነትን ለጌታ ለኢየሱስ ብቻ የተሰጠ አድርገን እንዳንመለከት በተለይ ቤተክርስቲያንን (የጌታን ህዝብ) ለመምራት በሃላፊነት ላይ ያለን መሪዎች የርሱን ምሳሌ እንድንወስድ ታዘናል። መልካም እረኛችን እርሱ ብቻ ነው እንደእርሱ ያለ መልካም እረኛ የለንም በማለት፤ ለእኛ የተሰጠንን ህዝቡን የመጠበቅ እና የመምራት ሃላፊነት ወደጎን ተወት ያደረግን እንደሆን የእረኞች እረኛ የሆነው ጌታ ይጠይቀናል።
በዘመናችን ያየናቸው እረኞች ሶስት አይነቶች ናቸው፦
1. የመንጋው ባለቤት
2. የመንጋው እረኛ
3. የመንጋው ነጋዴ
1- የመንጋው ባለቤት፡– እረኞች የመንጋው ባለቤት ለመሆን ይዳዳቸዋል። እረኞች መንጋውን የሚጠብቁ፣ የሚንከባከቡ የሚመግቡ እና የሚያሳድጉ ባለ አደራዎች እንጂ ባለቤት አይደሉም፡፡ የመንጋው ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ሾልከው የገቡ እረኞች እንዲህ አይነት ባህሪ ይታይባቸዋል።
2- የመንጋው እረኛ፡– የእረኝነት ልብና ጥሪ ያለው እርሱ የመንጋው እረኛ ይባላል። እንዲህ አይነት እረኛ መንጋዎቹ ሊያወሩት የሚፈልጉት፣ እርሱም ሁሉን ለመስማት የልብ ስፋት ያለው፣ ማስተማር፣ መምከር የመንጋውን ጤንነት መቆጣጠር የሚችል እርሱ የእረኝነት ጸጋ ያለው ነው፡፡ እረኛ የመንጋውን ባለቤት እያሰበ የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ይጥራል፡፡ ሕዝቡ የእግዚአብሔር ነው ብሎ፣ በደም ዋጋ የተገዛ የክርስቶስ ገንዘብ መሆኑን አስቦ የተሰጠውን አደራ ለመፈጸም ጠንቃቃ ይሆናል፡፡
3- የመንጋው ነጋዴ፡– የመንጋው ነጋዴ እረኞች መንጋውን የሚፈልጉት ለሥጋዊ ጥቅማቸው ብቻ ነው፡፡ የመንጋው ነጋዴዎች መንጋውን ሲመለከቱትም ሆነ ሲመግቡት መንጋው ከተመገበ በኋላ አድጎ ለእርድ እንዲደርስ ብቻ ያሳድጉታል፤ ከዚያም ሥጋው ይህን ያህል ቆዳው ይህን ያህል ያወጣል እያሉ ከመንጋው የሚያገኙትን ትርፍ ሲያሰሉና ሲተምኑ፤ ከመንጋው የሚያገኙትን ገቢ ሰብሳቢዎች ሆነው ይቀራሉ። ትርፍ ካስገኘላቸውም ደግሞ ለሌላ በላተኛ አሳልፈው ከመስጠትና ከመሸጥ ወደኋላ አይመለሱም። እነዚህ የመንጋው ነጋዴዎችም ሆኑ መንጋውን በባለቤትነት ለመያዝ የሚፈልጉ እረኞች ሌላ ስፍራ ላይ የሚያገኙት ጥቅም ካጋጠማቸው ወይም ደግሞ መንጋው የሚረባ(የሚወልድ/የሚበዛ) ወይም ዋጋ የሚያወጣ ካልመሰላቸው፤ መንጋውን ቀን ያሰማሩበት ሜዳ ላይ በትነውት መንጋው በአውሬ ይበላ አይበላ፤ ሲመሽ ወደ ማደሪያው በረት ይግባ አይግባ ግድ ሳይሰጣቸው/ሳይላቸው የሚፈረጥጡ አይነቶች ናቸው።
የእረኛ ባሕርያት (መገለጫዎች)
1. መጋቢ ነው፡– እረኛ ለምለሙን ሣር፣ ንጹሑን ውሃ እየፈለገ መንጋውን ይመግባል፡፡ አገልጋይም የጠራውን ቃለ እግዚአብሔር፣ ጤናማውን ትምህርት በመስጠት የምእመናንን ነፍስ ይመግባል፡፡
2. ጠባቂ ነው፡– እረኛ በጐቹን ከራሳቸው ሞኝነትና ከጨካኝ አውሬ ይጠብቃል፡፡ መጠበቅ አድካሚ መሆኑን የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ ምእመናን ያለባቸው ፈተና ሰይጣናዊ ብቻ አይደለም፣ የገዛ ሞኝነታቸውም ፈተናቸው እንደሆነ አውቆ ከራሳቸውም ሞኝነት ይጠብቃቸዋል፡፡
3. አካሚ ነው፡– እረኛ ገደል ገብታ የወደቀችውን ያወጣታል፣ ስብራቷን ይጠግናል፣ መራመድ ቢያቅታት ይሸከማታል፡፡ አገልጋይም በስህተትም ሆነ በድፍረት ለወደቁት ምእመናን ይራራል፡፡ ካሉበት ድረስ ሄዶም ሐፍረታቸውን ገፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመልሳቸዋል፡፡
4. አመጣጣኝ ነው፡– እረኛ ብርቱው ደካማውን እንዳይገፋው፣ ግልገሎች ከትልልቆች ጋር ሲጓዙ ኋላ እንዳይቀሩ ያመጣጥናል፡፡ ሁሉንም በእኩልነት መመገብ፣ ደካማና ብርቱውን በማያያዝ አብረው እንዲራመዱ አመጣጥኖ ያስኬዳል፡፡ ብርቱውን ብቻ የሚከተል ደካማውን ወደኋላ የሚተው እረኛ መሆን አይችልም፡፡
5. መሸከም፡– እረኛ የተሰበረችውንና ፍጥነት የሌላትን ግልግል ይሸከማል፡፡ አገልጋይም ብዙ ማባበል የሚፈልጉትን ምእመናንን መታገሥ፣ ዕድገታቸው ዘገምተኛ የሆኑትን በተስፋ መጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡ ሙሴ የሕዝቡን ድካም፣ ሸክም፣ ክርክር ተሸክሞ ነበር የሚመራው (ዘዳ. 1÷12)፡፡
6. ማሰማራት፡– እረኛ መንጋውን ያሰማራል፡፡ በቅርብ ርቀት ሆኖ ይከታተላቸዋል፡፡ አገልጋይ እረኛም ምእመናንን ማሰማራት፣ ሥራ መስጠት፣ እንዲያገለግሉ ማበረታታት አለበት፡፡
7. ስለ አንድ ይቆረቆራል፡– እረኛ ዘጠና ዘጠኝ በጐች ቢኖሩትና አንዲቱ ብትጠፋበት የሚበዛውን አትርፌአለሁ ብሎ አይተዋትም፡፡ ይፈልጋታል፡፡ አገልጋይም ስለ አንድ ነፍስ ግድ ሊለው ይገባል፡፡ የአንድ ነፍስ ዋጋን ያላወቀ አገልጋይ እረኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የብዙዎችም ዋጋ የክርስቶስ ደም ነው፣ የአንዲቱም ዋጋ ያው የክርስቶስ ደም ነው፡፡
8. በህብረት ይሰራል፦ እረኛ መንጎቹ በዝተው ለቁጥጥር እንዳያስቸግሩት መንጎቹን ከሚወዱና ከሚንከባከቡ ጋር አብሮ በመተባበር ይሰራል (ሙሴ በዘዳ 1፡12 ላይ ብቻውን ለመስራት ስላልቻለ ከምትመርጡት ሰዎች ጋር አብረን እንሰራልንና ሰዎችን ምረጡ አለ)
ማጠቃለያ
ጌታ ኢየሱስ ትልቅነት ማለት አገልጋይነት መሆኑን በተግባር ያሳየ መምህር ነው። ጌታ ኢየሱስ ሁሉም በእግሮቹ ስር የተገዙለት ጌታ ነው። እርሱ ጌታ ሆኖ ሳለ የኖረው ኝ እንደ አገልጋይ ነው። ትልቅነት ማለት አገልጋይነት እንደሆነ በኑሮው የገለጸ፤ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የዝቅተኝነትን ምሳሌነት ያሳየ እና ለደቀመዛሙርቱም የነገራቸው እርሱ እግር እንዳጠበ እነርሱም እግር እንዲያጥቡ ነው። ይህም “የአገልጋይነት” የዘወትር ልብሳቸው እንዲሆን ነው። መቼም ለእራት ከተሰበሰቡት መካከል እግር የማጠብ ተግባር የመምህሩ አይሆንም፤ የሌሎቹንም እግር እንዲያጥብ አይጠበቅበትም። ጌታና መምህር የሆነው ኢየሱስ “ለባሪያ/አገልጋይ” የ’ሚ’ተውን (‘ሚ‘ ጠበቅ ተደርጎ የሚነበብ) ስራ በመስራት የመሪነትን ምንነት በተግባር ያሳየ አስተማሪ ነው።
ጌታን በሚከተሉ ደቀመዛሙርት መካከል ማን ትልቅ እንደሆነ እርስ በርስ የተከራከሩበት ጊዜ ነበር። ጌታም “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤” ነበር ያላቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ስንመለከት፤ የጌታ አመራርና ጥበቃ ያተኮረው በቁጥር ብዛት ወይም በአብላጫ ላይ ሳይሆን በነፍስ ወከፍ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ ነበር። በበረት ውስጥ ካሉት በጎች አንዱ ቢጠፋ ከዘጠና ዘጠኙ አንጻር “ምንም” ባልሆነ ነበር። ጌታ ኝ ለአንዱ የሚጠነቀቅና እስኪያገኘው ድረስ የሚፈልግ እረኛ ነው።
ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲያደርግ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት በመሆኑ ከአምላኩ ርቆ ሊባዝንና ሊጠፋ አይገባውም ብሎ ፍለጋ መሄድ የእረኝነት ባህሪ ነው። እረኛ በበረት “የቀረው ይበቃኛል” የሚል ሳይሆን አንዱን የጠፋውን ፍለጋ እንደሚሄድ “ሁሉም ለጌታ ያስፈልጉታል” (ማቲ 18፡12 እስከ14) የሚል ሰው ነው። መልካም እረኛ በተሰማራበት ቦታ ሁሉ ለሰው ዋጋ የሚሰጥ፤ ለአንድ ለባዘነ፤ ለደከመ፤ ለጠፋ ግድ የሚለው ነው። በአንጻሩ ደካሞችን የሚያገል(የሚያሸሽ) ወይም በመጥፋታቸው የሚደሰትና ጥቂቶቹን ብቻ በታጠረ በረት ውስጥ ቆልፎ የሚይዝ መሪ የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ያለው አይደለም።
ጌታ ሲናገር “በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ” (ዮሃ 10፡27) አለ። እንዲሁም ስለመልካም እረኛ ሲያስተምር፡ “በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል፤ የርሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱን ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም። የሌሎችን ድምጽ አያውቁምና” (ዮሃ 10፡3 እስከ 5) አለ። ይህ በእረኛና በበጎች መካከል ያለውን መተዋወቅ፤ መቀራረብ፤ መተማመን ይገልጻል። እንዲሁም መሪ የሚመራውን ህዝብ የሚያውቅ ህዝቡም በአመራሩ በመተማመን የሚከተለው መሆን አለበት።
የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነት የሚከተል እረኛ በጎቹን በስም የሚያውቅና ከበረት የጎደሉም ሲኖሩ እንዲመለሱ ፈጥኖ የሚፈልግ ነው። በጎቹም ወደበረት እንዲመለሱ አስቀድመው የመሪውን ድምጽ የሚያውቁ ሊሆኑ ይገባል። ስለሆነም በመሪውና በተመሪዎች መካከል፤ በእረኛውና በበጎች መካከል የቀረበ ኝኙነትና ትውውቅ አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ ክርስቲያናዊ መሪነት መልካም እረኝነት የሚሆነው የጠፋው በተገኘ ጊዜ፤ የባዘነው በተመለሰ ጊዜ፤ የደከመው በተጽናና ጊዜ ነው። እንዲህ አይነቱ መሪ የክርስቶስ ልብ ያለው የባዘኑትን ፈልጎ የሚያገኝ ደስታውም በመመለሳቸው የሚሆንለት ሰው ነው። እግዚአብሄር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተዋጁትን ልጆቼ ያላቸውን ህዝቦቹን ለተቀጣሪ እረኛ አሳልፎ አይሰጥም፤ በአደራ የተቀበለውን ህዝብ፤ በበረቱ ውስጥ የገቡትን መንጋዎቹን (በጎችን፤ ጥቦቶችን እና ግልገሎችን) እንደራሱ ለማይመለከት፤ የጠባቂነት መንፈስ ብቻ ላለው ተቀጣሪ እረኛ አሳልፎ አይሰጥም። ኢዮብ መንጋዎቹን በውሾች (ኢዮብ 30፡1) ያስጠብቅ እንደነበረውም እግዚአብሄር ህዝቡን ለጯሂና ለተናካሽ ውሾችም አይሰጥም። አይተውምም።
መልካም እረኞችን ለማግኘት ምን እናድርግ ?
ቃሉ፡– “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ እረኛ እንደ ሌላቸው በጐች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው” ይላል (ማቴ. 9÷36-38)፡፡
የጌታችን ታላቅ ሀዘንና ታላቅ መመሪያ ነው፡፡ ሀዘኑ እረኛ አልባ መሆናቸው ነው፣ መፍትሄው መልካም እረኛ እንዲሰጥ እግዚአብሔርን መለመን፣ መጠየቅ፣ ማንኳኳት፣ ሁሌም ሳይታክቱ መጮህ ነው፡፡ እረኛ የሌለው መንጋ የሚባዝን፣ የማይሰባሰብ፣ ድንጉጥ ነው፡፡ ከመንጋው ፊት የሚሆኑ ቀድመው የሚታዩ እረኞች ያስፈልጉናል፡፡ እረኛ የሚገኘው ደግሞ ምእመናን ሲጸልዩ ከምእመናን ውስጥ ነው፡፡ ከልብ ካልጸለዩ መልካም እረኞች አይነሡም፡፡ መጨረሻው በመንጋው ነጋዴዎች መወረር ይሆናል፡፡
ምእመን ዛሬ ከፊት ከፊት እየሄዱ ስለሚመሩ ስለ መልካም እረኞች እየጸለይን ይሆን?
እረኞችስ ድርሻችንን እየተወጣን ይሆን ? የመንጋው ባለቤት ያያል ! ለእያንዳንዱ እንደስራው መጠን የሚከፍል ዋጋው በእርሱ ዘንድ ያለ ጌታ በቶሎ እመጣለሁ ይላል !
ጆሮ ያለው ይስማ !
ይህንን ጽሁፍ ወደውት ከሆነ ላይክ በማድረግ እንዲሁም ድህረ ገጹን ሰብስክራይብ ቢያደርጉ ሌሎች ጽሁፎች ሲለቀቁ ወዲያው እንዲደርስዎት ይሆናል። ለሌሎች በማካፈልም የድርሻዎትን ይወጡ። እንዲሁም ከታች ያሉት ዌብሳይቶች ላይ ያገኙኛል ሊንኩን በመጫን ይፈልጉኝ አመሰግናለሁ።
