የኤልያሴብና የጦቢያ ወዳጅነት ለመንፈሳዊ ኪሳራነት !

በነህምያ ዘመን እንዲህ ሆነ፡፡ ነህምያ የኢየሩሳሌምን መፍረስና የበሮችዋን መቃጠል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ አለቀሰም፡፡ ከዚያም ከንጉሡ ፈቃድ አግኝቶ ኢየሩሳሌምን ሊሰራ በመጣ ጊዜ ሶስት ጠላቶች ተነሱበት፡፡ “ሐሮናዊውም ሰንበላጥ ባሪያውም አሞናዊው ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፡፡ ቀላል አድርገውንም ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድን ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወዳላችሁን? አሉን፡፡” ይላል (ነህ.2፥19) ከዚህም ሌላ በብዙ ማስፈራራትና ዛቻ፣ በደብዳቤም በሰውም ኢየሩሳሌም እንዳትሰራ የነህምያን ልብ ለመስበር ሞክረዋል፡፡ ነህምያ ግን የአምላኩ እጅ ከርሱ ጋር ነበረችና ሥራውን ጨረሰ

    ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ግን የኢየሩሳሌምን መሰራት ሲቃወም የነበረው ጦቢያ መኖሪያ ፍለጋ ወደ መቅደሱ አዘገመ። ኤልያሴብ ከሚባለው ካህን ጋር በመወዳጀትም በእግዚአብሔር ቤት ጓዳ ለመቀመጥ ቻለ፡፡ ነህምያ ስለዚህ ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል“ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሹሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ ለሌዋውያንና ለመዘምራን ….. እንደ ህጉ የተሰጣቸውን ለካህናቱም የሆነውን የማንሳት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን  ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር፡፡» (ነህ.13፥4-6) ይህ መንፈሳውያን ለሆኑ ሁሉ ታላቅ መልእክት አለው፡- የኢየሩሳሌምን መታነፅና መታደስ በፅኑ ሲቃወም የነበረው ተቃዋሚ ጠላት ጦቢያ ከእግዚአብሔር ቤት ውስጥ  ታላቁን ጓዳ ሲያገኝና በዚያ ሲቀመጥ ለነህምያና ዛሬም የነህምያ መንፈስ ለሆነላቸው እንዴት የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ ነው ! ያውም የተሰጠው ታላቁ ጓዳ እንደህጉ ለሌዋውያን ለመዘምራን ለበረኞች ለካህናት በአጠቃላይ ለመቅደሱና ለታላቁ ንጉሥ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች የተዘጋጀው መብል የሚቀመጥበት የከበረው ቦታ ነበር፡፡ መብል በሚቀመጥበት ቦታ ውስጥ የእግዚአብሔር ህዝብ ጠላት ጦቢያ ተቀምጦ ነበር፡፡ ካህኑ ኤልያሴብ ለጦቢያ ይህንን የእግዚአብሄርን ጓዳ፤ የከበረውን ስፍራ ሊሰጠው አስቀድሞ ስፍራን ጠርጎለት(አመቻችቶለት) ነበር። ኤልያሴብ ያደረገው ክፉ ስራ ነበር፤ ለምን ? የእግዚአብሄርን ህዝብ ሊያስጨንቁ፤ የእግዚአብሄር ህዝብ አምላኩን እንዳያመልክ ኤልያሴብና ጦቢያ ተወዳጅተው ነበር ይለናል። አሁንም እኔ እና አንተ አንቺ በእግዚአብሄር ቤት ክፉ የሆነን ስራ ለመስራት የተወዳጁትን ካህኑን ኤልያሴብ እና ጦቢያን፤ ከክፉ ስራችሁ ተመለሱ ልንላቸው ይገባል።

   ዛሬም በዚህ ቃል ራሳችንን እና መቅደሳችንን ማለትም እግዚአብሄርን ማምለኪያና ህብረት ማድረጊያ ስፍራዎቻችንን እንዲሁም መንፈሳዊ ጓዳችንን እንፈትሽ፡፡ ከካህኑ ወይም ከሐሰተኛ አገልጋዮች ጋር ተወዳጅቶ የእውነት ዓምድና መሰረት በሆነው በእግዚአብሔር ቤት ጓዳ ውስጥ የተቀመጠውን የዘመኑን ጦቢያ ሃሰተኛና አስመሳዩን እንንቃበት፡፡ ይህም የዘረኝነት እና የግለኝነት ባህሪ (ቤተክርስቲያንን እንደግል ንብረት ማየት) የመጣላት የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት የሆነው አሮጌው ሰው(ጦቢያ) ነው። ባለንበትም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በተለይ አሁንም ጦቢያ “አሮጌው ሰው” ገዝፎ የሚታየው በታላቁ የአገልጋዮች የመዘምራን የሌዋውያን ጓዳ ነውና ነህምያዎች ሆይ ይህንን ጓዳ ለማፅዳትና ለእግዚአብሔር ለመቀደስ “ለመለየት” እንትጋ። 

   ነህምያ ያደረገውን ተመልከቱ “ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦቢያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ፡፡ እጅግም አስከፋኝ፡፡ የጦቢያንም የቤቱን እቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጭ ጣልሁ፡፡ ጓዳዎቹንም እንዲያነፁ አዘዝሁ፡፡ የእግዚአብሔርንም ቤት እቃዎች፣ የእህሉንም ቁርባን፣ እጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ” (ነህ.13፥7-9) ይህ መልእክት ለኛም በዚህ ዘመን ላለን የወንጌል መልእክተኞች የተሰጠ የአደራ መልእክት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቤት ጓዳዎች ውስጥ ከኤልያሴብ ጋር ተወዳጅቶ የእግዚአብሄርን ህዝብ የሚያስጨንቅ፤ ለህዝቡ ስቃይና ሃዘን እንዲሁም ጭንቀት ምንም አይነት ሃዘኔታ እና ርህራሄ የሌለውን ጨካኙን ጦቢያን ከኤልያሴብ ጋር ልናስወግደውና ልናፀዳ ይገባል፡፡ (ሮሜ.12፥1) ከጦቢያ፣ ከአሮጌው ሰው፣ ከስጋዊ ማንነት የፀዳ፣ የእውነት ዓምድና መሰረት የሆነውንም እውነተኛ የእግዚአብሔር መቅደስ ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ጦቢያ በተቀመጠበት ጓዳ የጠራና የሰባ የመንፈስ መብል (የሚያሳድግ የእግዚአብሄር ቃል) ስለማይገኝ ምዕመናን እንደሚገባ ማደግ አይችሉምና፡፡ 

    መንፈሳዊ ቤትን ለመስራት በመጀሪያ ጓዳን ማጽዳት አስፈላጊ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል ፡፡ ጓዳን ማጽዳት ስል ያለ እግዚአብሄር ጸጋ የሚያገለግሉ የሚያስተምሩ የሚሰብኩ የሚዘምሩ እረኛ፣ ነብያት፣ ሃዋርያት እና ዘማሪ የሆኑ እነዚህን ለይተን ማጽዳትና ጸጋው ያላቸውን መተካት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ቤቱ አዲስ ሲሆን ልንረሳው የማይገባን ነገር ከአሮጌ ቤት አሮጌ እቃ ለቤቱ እንደማይመጥነው ለአዲሱ መንፈሳዊ ቤትም በአዲስ ቅባት የተቀቡ ለቤቱ የሚመጥኑ የመገልገያ እቃዎች ያስፈልጋሉና፤ ነህምያዎች ነቅተን እንድንለይና ቤቱን እንድናሳምረው ያስፈልጋል።

      ሌላው ደግሞ ዛሬ ጦቢያ ሆኖ በቤተክርስቲያን የተቀመጠ አላፈናፍን ያለና የእግዚአብሄርን መንፈስ ያዳፈነ፤ በጥንቱ ቤታችን የነበረ ዓይነት የበዓል (የዓመቱ ገብርኤል፣ ሚካኤል፣ ማርያም ወዘተ ) አከባበር እኛም ቤት ( የእናቶች የአባቶች የወንድሞች የእህቶች የፓስተሮች ቀን) ብዛት ይሆን ? የእግዚአብሄር ህዝብ ሆይ ዓይናችንን፣ አስተሳሰባችንን እና ልባችንን ከኢየሱስ ላይ እንድናነሳ የሚያደርጉንን ኤልያሴብን እና ጦቢያን ነቅተንባቸው ሃሳባቸውን ለይተን እንድንመታው ይገባናል፡፡

ተባረኩልኝ፡፡

ካሱ ቦስተን 

    ይህንን ጽሁፍ ወደውት ከሆነ ላይክ በማድረግ እንዲሁም ድህረ ገጹን ሰብስክራይብ ቢያደርጉ ሌሎች ጽሁፎች ሲለቀቁ ወዲያው እንዲደርስዎት ይሆናል። ለሌሎች በማካፈልም የድርሻዎትን ይወጡ።

እንዲሁም ከታች ባሉት ሌሎች ዌብሳይቶች ላይ ያገኙኛል ሊንኩን በመጫን ይፈልጉኝ አመሰግናለሁ።

linkedin.com/in/kassuboston

https://www.facebook.com/kasselsa97

https://thelastbelldotcom.wordpress.com

https://www.instagram.com/kasselsa97

https://www.youtube.com/channel/UCXQeAJgDLecjaAb_7ZjJmoA

Leave a comment