ቤተክርስቲያን ሆይ ንቂ ! ዛሬ ቤ/ክ የትኛውን ትመስል ይሆን ?

 ቤተ ክርስቲያን ከመሰረታትና ሙሉ ባለቤትነት ካለው ከክርስቶስ ተልዕኮ ተሰጥቷት በምድር ላይ ያለች የክርስቶስ አካል ነች፣ ቤተክርስትያን ላለፉት 2000 አመታት በብዙ ድልና በብዙ ውጣ ውረድ እንዲሁም በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፋለች አሁንም እያለፈች ነው። ቤተክርስቲያን የሰው አይደለችም፣ የሐዋርያ፣ የፓስተርም፣ የነብይም፣ የወንጌላዊም፣ የአስተማሪም አይደለችም፤ ነገር ግን ሰው ሊያስተዳድራት ይችላል። 

     ቤተ ክርስቲያን የራሱ የእግዚአብሄር ሆና ሰዎችን ግን የተለያየ ጸጋና ስልጣንን በመስጠት ያስተዳድሯት ዘንድ በውስጥዋ አስቀምጧል። እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን ሁላችንም ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄር ናት ብለን ዝም እንድንል አይጠበቅብንም። በውስጧ ስንመላለስ በስርዓት እንወጣና እንገባ ዘንድ፤ እንዲሁም እግዚአብሄር በሰጠንም ጸጋና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እናገለግል ዘንድ፤ በቤቱ ውስጥ የሚያስቀምጣቸው ቤቱን እንዲመሩ ስልጣንን የሰጣቸው ሰዎች: የሰዎችን ጸጋ በማየት እንደስጦታቸው እንዲያገለግሉም ሊያደርጉ የሚገባቸው በመሪነት ቦታ ያሉ ሰዎች ናቸው ማለት ነው። እግዚአብሄር መጥቶ ቤቱን እንዲጠብቅ የምትመኙ ካላችሁ ተሞኝታችኋል። 

     መጽሐፍ ቅዱሳችን ቤተክርስቲያን ለሰራችው መልካምም ሆነ እንደ እግዚአብሔር ቃል ባልተመላለሰችበት ጉዳይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ብድራትን እንደምትቀበል ያስተምራል፤ ቤተክርስቲያን በአገልግሎቷ፣ በአካሄዷ፣ በሃላፊነቷ፣ በተሰጣት የጸጋ ስጦታና በተሰጣት መንፈሳዊ ስልጣንና ኃይል ጉዳይ በኢየሱስ ክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ትቆማለች፣ በዚህ የፍርድ ወንበር ፊት ትዳኛለች ትጠየቃለች፣ ከዛም እንደስራዋ ታገኛለች።

  ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። ሮሜ 14፡10

እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። ሮሜ 14፡12

     ጌታ ኢየሱስ ለዮሃንስ ራእይ 1፡11 ላይ እንዳዘዘው፦ “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ።”  እንዳለው የራዕይ መጽሃፍ ያሳየናል። 

❄ 👉 እነዚህ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በወቅቱ በትንሿ እስያ የሚገኙ አጥቢያዎች ነበሩ፤ እያንዳንዳቸው አብያተ ክርስቲያናት ጠንካራና ደካማ ጎኖች ነበራቸው፣ ኢየሱስም ለጠንካራ ጎናቸው ማበረታቻ፤ ለደካማ ጎኖቻቸው ደግሞ ምክር ሲሰጥና ሲገስጽ እንመለከታለን። ዛሬም በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የምናየው እኛ ያለንበትን የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተክርስቲያን ይሆናል። ዛሬም እንደዮሃንስ በመንፈስ የሚመራ ሰው ቢኖር ከጌታ ዘንድ በቦስተን ላለችው የኢትዮጵያ ወንጌላዊ ቤተክርስቲያን እንዲህ ብለህ ጻፍና ላክ ቢባል ምን አይነት መልዕክት ይላክላት ይሆን ? እኔ ይህን ይህን ለማለት ባልችልም በተጻፈው በራዕይ መጽሃፍ ውስጥ ያለውን ካየን፤ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና እንቀበለዋለን።  

 1 👉 የኤፌሶን ቤተክርስቲያን (ራእይ 2፡1-5)

    የኤፌሶን ቤ/ክ ስንመለከት የኤፌሶን ቤ/ክ ለክርስቶስ ስም ስትል ጸንታ የቆመች፣ ሐዋርያት ነን ባዮችን መርምራ ሐዋርያት አለመሆናቸውን የምታጋልጥ፣ ያልደከመች ቤ/ክ ነበረች፤ ግን የቀድሞ ፍቅሯን ትታለች፣ ለዚህም ውድቀቷ ከወዴት እንደ ወደቀች እንድታስብ ንስሐም እንድትገባ የቀደመውን ሥራዋን እንድታደርግ፤ አለዚያ ጌታ እንደሚመጣባት ንስሐም ባትገባ መቅረዝዋን ከስፍራው እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ደርሷታል። ራእይ 2:1-5 የኤፌሶን ቤ/ክ በወቅቱ በትንሿ ኤስያ የምትገኝ ከተማ ነበረች፣ ኤፌሶን የንግድና ከሶስቱ የሮም ግዛቶች በጣም ዝነኛ ነበረች፣ ኤፌሶን ከተማ የአርጤምስ ቤተ ጣኦት መገኛም ነበረች (ሐዋ 19:21-41)

2 👉 ሰምርኔስ ቤተክርስቲያን (ራዕ 2፡9)

   የሰምርኔስ ከተማ ከኤፌሶን በስተምዕራብ በኩል በ25 ማይል ርቀት ትገኝ ነበር፤ በዚህ ከተማ ቤ/ክ ከሁለት ዋና ዋና ችግሮች ጋር ትጋፈጥ ነበር 1ኛ የአይሁድ ክርስትናን መቃወምና አይሁድ ያልሆኑ አምልኮተ ንጉስን መቀበላ ቸው ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ።

3 👉 የፔርጋሞን ቤተክርስቲያን

   የፔርጋሞን ከተማ በ1000 ጫማ ከፍታ ባለው ከተማ ላይ የተመሰረተች ከተማ ነበረች፣ ከተማዋ የግሪክ ባህልና ስልጣኔ ማዕከል ነበረች፣ ከተማዋ የተለያዩ አይነት ጣኦቶች ነበሩባት፣ ፔርጋሞን በእባብ ራሱን በመሰለ ጣኦት የተሞላች ከተማ ነበረች፤ አማኞች በዚህ ከተማ ታላቅ ስደትና እምነታቸውን እንዲተው ግፊት ይደረግባቸው ነበር፣ በፔርጋሞን ይገኙ የነበሩ አማኞች በእምነታቸው ተመስክሮላቸዋል የተወቀሰችበትም ነገር አለ አንደኛ በስህተት ትምህርትና በስነምግባር ጉድለት።

4 👉 የትያጥሮን ቤተክርስቲያን (ራዕ 2፡20-22)

    ትያጥሮን ጥንት በሮማውያን የኤዥያ ግዛቶች ውስጥ አንዷ የነበረች ባለጠጋ ከተማ ነበረች። ይህች ከተማ በአሁኑ ወቅት ቱርክ ነች። ለዚህች ቤ/ክ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠንካራ እና ደካማ ጎኗን በማንሳት ከደከመችበት ሁኔታ እንድትወጣ አምላካዊ ምክር ሲመክርና ሲገስጽ እናነባለን።

  የትያጥሮን ቤተክርስቲያን 5 ዋና ዋና ጠንካራ ጎኖች

1 > ፍቅር  

2 > እምነት  

3 > አገልግሎት 

4 > ትዕግሥት  

5 > ታላቅ ስራ

   በመቀጠል ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህችን ቤ/ክ ሃጢአት/ውድቀት ይጠቅሳል።

    “ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተም ረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ”

👉 በወቅቱ ሐሰተኛ ነብያቶች፣ ጣኦት የሚያመልኩ፣ ግልሙትና ውስጥ የገቡ ክርስቲያኖች በቤተክርስትያን ውስጥ ነበሩ።

5 👉 የሰርዴስ ቤተክርስቲያን (ራዕ 3፡1-2)

   የሰርዴስ ከተማ በወቅቱ ባለጠጋ የንግድ ከተማ እና በሙስና የምትታወቅ ከተማ ነበረች። 

የሰርዴስ ቤ/ክ ዋና ችግር 👇

ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና። (ራእይ 3፡2)

6 👉 የፊልድልፊያ ቤተክርስቲያን(ራዕ 3:8-9) ⛪

    የፊልድልፊያ ከተማ በፔርጋሞን ህዝቦች የተመሰረተች ከተማ ነበረች ከተማዋ ከዘመናት በኋላ በመሬት መንቀጥቀጥ ልትጠፋ ችላለች፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህች ቤ/ክ ማበረታቻ እና ዋና ዋና ምክሮችን ይመክራታል።

7 👉 የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን (ራዕ 3:16-17)

   የሎዶቅያ ከተማ በባንክ ስልጣኔና በጥጥ ንግድ እንዲሁም በህክምና ት/ት በተለይ በአይን ኩል ገናና ነበረች፣ የቤ/ክ ዋና ችግር የአቋም ችግር ነበር። ወይ ቀዝቃዛ አልሆነች ወይ ሙቅ/ትኩስ/ አልሆነችም ነበር። ሌላው የዚህች ቤ/ክ ድክመት ሃብታም ነኝ አንዳች አያስፈልገኝም ባይ መሆኗ ነው፣ ቤ/ክ ይህን ትበል እንጂ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ይላታል ። “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥” (ራእይ 3፡17)

⛪ ከላይ በራዕይ መጽሐፍ ላይ ከተመለከትናቸው ሰባቱ አብያተክርስቲያናት እኛ ምን እንማርባቸዋለን ?? ⛪

  1. ➡️ፍቅር ላይ ያልተመሰረተ አገልግሎት፣ እምነት፣ ጽናት፣ ትጋት ከንቱ እንደሆነ እንማራለን።⛪
  2. ➡️ቤ/ክ ለሰራችው ድልም ሆነ ሽንፈት ከኢየሱስ የምትቀበለው ብድራት እንዳለ መማር እንችላለን። ⛪
  3. ➡️ቤ/ክ ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጣት አላማ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባት እንማራለን።⛪
  4. ➡️ቤ/ክ የእምነት ተጋድሎን በሚገባ መታገል እንዳለባት መማር እንችላለን ⛪
  5. ➡️ቤ/ክ በአስተምህሮ፣ በአካሄዷ፣ አቋም ያላት የጸናች መሆን እንዳለባት መማር እንችላለን። ⛪
  6. ➡️ቤ/ክ የትኛውንም አይነት የዲያብሎስን አሰራር መቃወም እንዳለባትና በምንም ሁኔታ እና እንቅስቃሴዎች መተባበር እንደሌለባት ⛪
  7. ➡️ቤ/ክ ከመንግሥት፣ ከቤተሰብ፣ ከግለሰብ የተለያዩ አይነት ተቃውሞ ሊደርስባት ይችላል ቢሆንም ግን ጌታ እንደተናገረን መፍራት እና ወደ ኋላ ማፈግፈግ እንደሌለብን እንማራለን። ⛪
  8. ➡️ቤ/ክ የሃሰት ትምህርቶችን በመቃወም ጤናማውን ትምህርት መከተል እንዳለባት ያስተምረናል። ⛪
  9. ➡️የተለያዩ አጋንንታዊ ልምምዶች ቤተክርስቲያን ልትቃወም ይገባታል ለምሳሌ በፔርጋሞን ቤ/ክ በወቅቱ ፈውስ ለመቀበል በተሳሳተ ትምህርት ራሱን አዳኝ ነኝ ብሎ ወደ ሚጠራው እባብ ይሄዱ ነበር። ⛪

⛪ ቤተክርስቲያን መጠንቀቅ ያለባት አደጋዎች ⛪

    ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን ከሰዱቃውያን፣ ከዘረኝነት እና ከኤልዛቤል መንፈስ ልትጠነቀቅና ልትርቅ እንዲሁም መንጋዎቿን ልታስተምር እና ልታነቃ ይገባታል። እስኪ እነዚህን ሰፋ አድርገን እንመልከታቸው፤ 

🚫 1. 👉 ከዘመኑ ሰዱቃውያን

    የሰዱቃውያን ታሪካዊ አመጣጥ

        ሰዱቃውያን በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምድር የአገልግሎት ዘመን መኳንንቶች፣ ባለጠጋና የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ። በወቅቱ እስራኤል በሮማዊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ነበረች። ሰዱቃውያን ሰርኧዲን በሚባል ምክር ቤት ውስጥ 70 መቀመጫ ነበራቸው፤ ሰዱቃውያን በእስራኤልና በሮማውያን መካከል ሰላምና መልካም ጉርብትና እንዲኖር የሚሰሩ በላይኛው እርከን (Upper Class) ላይ የሚገኙ ቡድኖች ነበሩ።

        ሰዱቃውያን የእስራኤል ሊቀ ጳጳሳት የበላይ መሪዎች በመሆን ህዝቡን በሃይማኖትም በፖለቲካም ያገለግሉ ነበር፤ ሰዱቃውያን አምስቱን በሙሴ የተጻፉትን መጽሐፍት ብቻ ነበር የሚቀበሉት ሌላውን የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻህፍት አይቀበሉም። ሰዱቃውያን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ቀንደኛ ተቃዋሚዎች ነበሩ፣ ሲሰብክ ስብከቱን ይተቻሉ፣ ተአምር ሲሰራ በአጋንንት ስም ነው አጋንንት የሚያወጣው ይላሉ፣ ሲፈውስ አይቀበሉም፣ የእነርሱ ስራ የመንፈስ ቅዱስን ስራ ዝም ብሎ መቃወም ነው፤ ነገር ግን ሃይል አልባ የሃይማኖት ስልጣናቸው፣ ተቃውሟቸው በኢየሱስ ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም ነበር፣ በዚህም ዘመን የሰዱቃዊያን አይነት ማንነት ያላቸው አልጠፉም፣ አገልጋዮችን የማሳደድ ፕሮግራም እና ስትራቴጂ አውጥተው የሰይጣን ቀኝ እጅ የሆኑ በየመንደሩ በየህብረቱ እና በየቤተክርስቲያን ውስጥ የተሰገሰጉ እውነተኛ ወንድሞች የሚመስሉ ነገር ግን ያይደሉ የአምልኮ መልክ ያላቸው ኃይሉን የካዱ ብዙዎች ናቸው። እነዚህን ደግሞ መንጥሮ መለየትና ማውጣት ወደ እውነት እንዲደርሱ እውነትን ማስተማር እና መመለስ፤ ካልተመለሱ ደግሞ መለየት እንዲሁም መ-ለ-የት ያስፈልጋል ማለት ነው። 

    “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።” 2ጢሞ 3፡5

    የዘመኑ ሰዱቃውያን አነጣጥረው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚቃወሙት 8ቱን ዋና ዋና ነገሮችን እንመልከት፦

    1. ➡️የነብያትን አገልግሎት ከቤተክርስትያን ውስጥ ማዳከም፤
    2. ➡️የፈውስና የተአምራት አገልግሎቶችን ማናናቅ፤
    3. ➡️አጋንንት የማውጣት ስጦታዎችን የውሸት ትእይንት አድርጎ መስበክ፣ ማውራት፣ ማናፈስ፤
    4. ➡️አምስቱን ቢሮዎች ከቤተክርስቲያን ውስጥ አስወግዶ ቤ/ክንን ባዶ ማድረግ፣ (ሐዋርያ፣ ነብይ፣ መጋቢ፣ አስተማሪ፣ ወንጌላዊ)፤
    5. ➡️ከመንፈስ ቅዱስ ሃሳብ ጋር የማይሄድ አስተሳሰብ እና አመራር በቤ/ክ ውስጥ መዘርጋት፤
    6. ➡️ሀይል አልባ ቲኦሎጂ ማስፋፋት፤
    7. ➡️ትንቢትን መናቅና ማናናቅ፤
    8. ➡️ሚዛናዊነት የጎደለው አመለካከትን ማስፋፋት ነው።

    🚫 2. 👉 ከዘረኝነት

    ዘረኝነት በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲገባ የሚከሰቱ 12 ዋና ዋና አደጋዎች:-

    1. ➡️ቤ/ክ ሰማያዊ የሆነውን፣ ከሰማይ የተቀበለችውን አዲሱን ማንነት ትታ ስጋዊ በሆነው ምድራዊ ማንነት ብቻ በመመላለስ አዱሱን ፍጥረት ችላ ማለት ውስጥ ትገባለች። 
    2. ➡️ቤ/ክ ትልቁን የክርስቶስ ኢየሱስን ተልእኮ ጥላ/ዘንግታ በራሷ የስጋ ጉዳይ መጠመድ ትጀምራለች።
    3. ➡️አሮጌ ፍጥረት/ስጋዊነት በቤተክርስቲያን ውስጥ ይሰለጥናል።
    4. ➡️ቤ/ክ መንፈሳዊ ስልጣኗን እንዳትጠቀም አቅም ታጣለች።
    5. ➡️ቤ/ክ ቅዱስ ፍሬ ማፍራት ትታ የስጋ ስራዎች ውስጥ ትጠመዳለች።
    6. ➡️ቤ/ክ ሰዎች እንዳይድኑ መሰናከያ ልትሆን ትችላለች።
    7. ➡️የእግዚአብሔርን ቁጣ ትቀሰቅሳለች።
    8. ➡️ቤ/ክ ንጹህ አምልኮ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ይሳናታል።
    9. ➡️ቤ/ክ መፈራረስ ውስጥ ትገባለች።
    10. ➡️በዘረኝነት ላይ ያተኮረ አደረጃጀት፣ አስተምህሮ፣ ስብከት፣ አገልግሎት እና ወዳጅነት ላይ ትወድቃለች።
    11.  ➡️በመጨረሻው ቀን ከስራ ሽልማት ትጎድላለች።
    12. ➡️ቤ/ክ የሃይልና የስልጣን አካል/ድርጅት ከመሆን ይልቅ ባዶ ትሆናለች።

    የራዕይን መልዕክት ለምታነብ በዚህ ዘመን ላለች የክርስቶስ አካል ለሆነች ለቤተክርስቲያን መልዕክቱ ተመሳሳይ ሲሆን መልካም ላደረገችበት እሰየው የሚያሰኝ ሲሆን መልካም ላላደረገችበት ላጠፋችበት እንደአጥቢያ ቤተክርስቲያን ግሳጼውን ተቀብላ ንስሃ መግባት እንዳለባት ማወቅ ይገባታል። ቤተክርስቲያን ሁሌም መንጋዎችዋን ይዛ በንስሃ ወደጌታ መቅረብ አለባት። አሁን እንደምናየው ግን የንስሃ ትምህርቱም ሆነ የንስሃ ጸሎቱ በቤተክርስቲያን የቀረበት ሁኔታ ይታያል።

    🚫 3. 👉 የኤልዛቤል መንፈስ እና አሰራሯ

       “በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።

    ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።” (ራዕይ 2:18-23)  

      በመጽሃፍ ቅዱሳችን ሰይጣን በተለያየ መንገድ እንደሚገለጥ እና እንደሚመሰል የምናይባቸው ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ በእንሰሳት ሲመሰል፦ በእባብ፣ በዘንዶ፣ በጊንጥ፣ በአንበሳ፣ እና በሌሎችም እንስሳት ይመሰላል። በሰው ሲመሰል ደግሞ በኤልዛቤል እንደሚመሰል ከላይ ያየነው የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍላችን ያሳየናል። ኤልዛቤል ማነች የሚለውን እስኪ እንመልከት፦  

    👉 ኤልዛቤል ማነች ????

        ኤልዛቤል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 23 ጊዜ የተጠቀሰች ሲሆን 22 ጊዜ በብሉይ ኪዳን 1 ጊዜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሳለች። ኤልዛቤል ከጣዖት አምላኪ ቤተሰብ የተወለደች ጣኦት አምላኪ ነች፤ መጽሃፍ ቅዱስ ኤልዛቤልን ሐሰተኛ አስተማሪ ወይም አሳች አድርጎ ያሳየናል። የሲዶናዊያን ንጉስ የኤትበአል ልጅ ነበረች። አባቷ ኤትበአል የበአል አምልኮ ተከታይ ነበር። ኤልዛቤል የእስራኤላውያን ንጉሥ የሆነው የአክአብ ሚስት ነበረች። ኤልዛቤል እና አክአብ ወደ ንግስና ከመጡ በኋላ ለእስራኤላውያን የውድቀት እና የመንፈሳዊ ጨለምተኝነት፣ የሞራል ውድቀት ምክንያት ሆነዋል። ባልዋ በአልን እንዲያመልክ እና ክፋትንም እንዲያደርግ የገፋፋች፤ የበአል ነብያትን የምትቀልብ እና የእግዚአብሄርን ነብያት ግን ትገድል የነበረች እንዲሁም ኤልያስ የበአልን ነብያት ስላስገደለ በእርሱ ላይ ዛቻን የተናገረች እና ናቡቴንም ያስገደለች ነበረች። በመጨረሻም በኢዩ ትእዛዝ ከመስኮት ላይ የተፈጠፈጠች መሆኗን መጽሃፍ ቅዱስ ይነግረናል።

         ምንም እንኳን ኤልዛቤል በመስኮት ተፈጥፍጣ የተገደለች ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ መንፈሷ በምድር ላይ ባሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ በስፋት እየሰራችና ክርስቲያኖችን በተለይ አገልጋዮችን እያሳተች ትገኛለች። በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ የዳነ ክርስቲያን ወደዘላለም ቤቱ እስኪሄድ ድረስ በምድር ላይ መንፈሳዊ ውጊያ ያካሂዳል። ይህ ውጊያ ከደም እና ከስጋ ጋር ሳይሆን መንፈሳዊ ውጊያ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በመንፈስ የሚደረግ እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ የሚደረግ ውጊያ አይደለም። እንደ አማኝ በምድር ላይ አሸናፊዎች፣ ብርቱዎች፣ ገዢዎች፣ አስፈሪዎች፣ ሆነን በክርስቶስ ተፈጥረናል። የተደረግነውን ማንነት በመጠቀም የዲያብሎስን ስራ ማፈራረስ የቤተክርስቲያን ድርሻ ነው። መንፈሳዊ ውጊያ የምናደርገው ሰይጣንን ለማሸነፍ ሳይሆን አሸናፊነታችንን ተጠቅመን በጨለማ ግዛት ያሉትን ሰዎች ለመታደግ ነው። ቤተክርስቲያን የአለም ብርሃን እና የምድር ጨው በመሆን የሰይጣንን ስራ በማፍረስ የእግዚአብሔርን መንግስት እንድታስፋፋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሃይል፣ ክብር እና ስልጣን ተቀብላለች።

    የኤልዛቤል 16ቱ ዋና ዋና መገለጫዎቿ

    1. 👉 ጣኦት አምላኪ ሴት ነች
    2. 👉 ነፍሰ ገዳይ ሴት ነች
    3. 👉 የባልን ራስነት የማትቀበል ሴት ነች
    4. 👉 ልበ ደንዳና ሴት ነች
    5. 👉 ጋለሞታ ሴት ነች
    6. 👉 ባለቤቷን የምትነዳ ሴት ነች (1ነገ 20:25)።
    7. 👉 ክፉ መካሪ ነች
    8. 👉 ስነምግባር የሌላት ሴት ነች
    9. 👉 መተተኛ ሴት ነች
    10. 👉 ጨቋኝ ንግስት ነች
    11.  👉 ሐሰተኛ ነብይ ነች
    12. 👉 ሐሰተኛ አስተማሪ ነች
    13. 👉 ሴረኛ ሴት ነች
    14. 👉 ነብያትን የምታሳድድ ጠላት ነች
    15. 👉 ራስ ወዳድ ሴት ነች
    16. 👉 ፍትህ የምታጣምም ሴት ነች።

    “ዳሩ ግን። ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ (ራእይ 2:20)

    ⛔️✴✴ የኤልዛቤል አላማዋ ✴✴⛔️

    1. የእግዚአብሔርን ህዝብ ለጣኦት እንዲገዙ እና እንዲሰግዱ ማድረግ።
    2. የእግዚአብሔር ህዝብ እንዲጎለትምቱ እና እንዲሴስኑ ማድረግ።

    3. የእግዚአብሄርን ህዝብ የሃሰትን ትምህርስት በማስተማር ከዓላማቸው ማሳት።

    👉 ኤልዛቤል ጋለሞታ ሴት ነች።


    ⛔️👉 የጋለሞታይቱ ሴት ባህሪዋ እና ምልክቶቿ ፦  ( ምሳሌ 7 )⛔️
    💢 ኤልዛቤል የተለየች ሆና ሰውን ሁሉ ለማጥመድ የምትችልበት የአለባበስ ዘዴ አላት፤  “እነሆ፤ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች።” (ምሳሌ 7፡10)

    💢 ኤልዛቤል ዘዋሪ እና አጥፊ ነች፤  “ሁከተኛና አባያ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም።” (ምሳሌ 7:11)
    💢 ኤልዛቤል አ’ዳ’ኝ (የም’ታ’ድ’ን) ሴት ነች፤  “አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች።” (ምሳሌ 7፡12)
    💢 ኤልዛቤል ከማንም ጋር አካላዊ ንኪኪ ትወዳለች፤ “ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው።” (ምሳሌ 7፡13)
    💢 ኤልዛቤል ማንንም አታፍርም፤ “ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው።”(ምሳሌ 7፡13)
    💢 ኤልዛቤል እቤት አትቀመጥም እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤ መዞር ትወዳለች፤ “እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም።” (ምሳሌ 7፡11)
    💢 ኤልዛቤል ስለ ህይወት ደንታ ቢስ ነች፤  “እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው።” (ምሳሌ 5፡5)
    💢 ኤልዛቤል ጥፋቷን የማትቀበል አማፂ ነች፤  “እንዲሁ በልታ አፍዋን የምታብስ። አንዳች ክፉ ነገር አላደረግሁም የምትልም የአመንዝራ ሴት መንገድ ናት”  (ምሳሌ 30፡20)
    💢 ኤልዛቤል ሃይማኖታዊ ሆና መታየት ደስ ይላታል፤  “መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ” (ምሳሌ 7፡14)
    💢 ኤልዛቤል ገዳይ ነች፤  “ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው። (ምሳሌ 7፡26)
    💢 ኤልዛቤል ሙልጭልጭ እና ብልጣ ብልጥ ነች።
    💢ኤልዛቤል ውበቷን በመጠቀም ታጠምዳለች፤  “ውበትዋን በልብህ አትመኘው፤ ሽፋሽፍትዋም አያጥምድህ።” (ምሳሌ 6፡25)
    💢ኤልዛቤል በንግግር ታጠምዳለች፤ “ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና።” (ምሳሌ 5፡3)
    💢ኤልዛቤል ለወሲብ ግብዣ ታደርጋለች፤  “ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን።” (ምሳሌ 7፡18)

     ⛔️ የኤልዛቤል አስተምህሮ ⛔️

    ቤተክርስቲያን ነቅታ ልትጋደል የሚገባት ሌላኛው የዘመኑ ተግዳሮት የኤልዛቤል አሰራርና አስተምህሮ ነው።

    አስተምህሮዎቿ ምን ይመስላሉ ?

    1. 👉 ድህረ ዘመናዊነት/postmodernism ይህ አስተሳሰብ እና ፍልስፍና በአንድ መንገድ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች የሚገለጽ ነው። ለምሳሌ በስነጽሑፍ፣በዘፈን፣በፊልም፣በፋሽን ፣በቴክኖሎጂ፣በትምህርት እና በማህ በራዊ ሚዲያዎች የሚቀነቀን ወይም የሚሰበክ የኤልዛቤል አስተ ምህሮ ነው። ድህረ ዘመናዊነት/postmodernism አለም አቀፍ እውነት የለም ብሎ የሚያምን ዘመናዊ አመለካከት ነው። እውነት የሚባለው ሰዎች የተስማሙበት እንጂ በራሱ የቆመ ነገር አይደለም ይላሉ።በዚህ አስተምህሮ እውነት ፍጹም ሳይሆን አንጻራዊ፤እውነት በቦታ፣ በሁኔታ በጊዜ ምክንያት የሚለዋወጥ ነው።

      ✳👉 ድህረ ዘመናዊነት/postmodernism/ በክርስትና ላይ ያመጣው ተጽእኖ

      ✔አለማዊነት

      ✔ቁሳዊነት

      ✔ሰውን ያማከለ አመለካከት መስበክ

      ✔ፍትወትን ማስፋፋት።

      ✔ሳይንስን የሁሉ ነገር ምንጭ ማድረግ

      ✔የፍቅር መቀዛቀዝ።

      ✔የእግዚአብሔርን ቃል ከዓለም ጋር ማቻቻል።

      💢ይሄ ሁሉ በዘመናችን ቤተክርስቲ ያን በግልጽ እያየን ያለ የኤልዛቤል አስተምህሮ ውጤት ነው። በአለም ላይ ያለች ቤተክርስቲያን የተለያዩ የሐሰት ትምህርት እየተገዳደራት ይገኛል።

      ⛔️ ሌሎች የኤልዛቤል ትምህርቶች ⛔️

      2. 👉አምላክ የለሽነት atheism፦ ይህ አስተምህሮ ሰው ሊያምን የሚገባው የሚታየውን እና የሚዳሰሰውን ብቻ ነው ብሎ ያስተምራል።

      3. 👉 ዳርዊኒዝም/ Darwinism /ኢቮሊሽነሪ ቲዎሪ) ፦ ይህ አስተምህሮ እግዚአብሔር መኖሩን ይክዳል፣ እውነት በሳይንስ መረጋገጥ አለበት ይላል። አምላክ የለም፣ ሰው ከእንስሳ የተገኘ እንስሳ ነው ይላል ።

      4. 👉ናቹራሊዝም / naturalism ፦ ይህ የኤልዛቤል አስተምህሮ የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን በምድር ላይ ማድረግ አለበት ይላል ።

      5. 👉 ማቴሪያሊዝም/ materialism ፦ ይህ አስተምህሮ ማንኛውም እውነት መረጋገጥ ያለበት ለፊዚክስ ቅድሚያ በመስጠት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ነው ብሎ ያስተምራል። 

      ⛔️✴ማጠቃለያ✴⛔️

             ወንድሞቼ እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው በሙሉ የኤልዛቤል መገለጫዎችና ባህሪዋን እንዲሁም ምልክቷን እና አስተምህሮዋን ስንመለከት፤ ዛሬ በምድር ላይ ያለች ቤተክርስቲያን አቅሟን ያጣችበትና የደከመችበት፤ ለምድር ጨው መሆን ያቃታት፤ ለዓለም ብርሃን መስጠት የማትችል ደካማ የሆነችበት፤ ወደዓለም ልትሄድና ወንጌልን ለማያምኑት ለመስበክ አቅምን ያጣችበት፤ ዓለም እራሷ ከነስርዓቷ እና ከነኮተቷ ቤተክርስቲያን ዘልቃ መድረክ የያዘችበት እና የእውነትን ወንጌልን አሽቀንጥራ በመጣል፤ ወንጌሉን አንግባ ሃሰትን የምትናገር ሆናለች። ስለዚህ ወገኖቼ የኤልዛቤልን መንፈስ ከቤተክርስቲያን መድረክ ላይ አንስተን በመስኮት አሽቀንጥረን ልንፈጠፍጣት ይገባል እላለሁ።  

          በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ የዳነ ክርስቲያን ወደ ሰማይ እስከሚሄድ ድረስ በምድር ላይ መንፈሳዊ ውጊያ ያካሂዳል።ይህ ውጊያ ከደም እና ከስጋ ጋር ሳይሆን መንፈሳዊ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በመንፈስ የሚደረግ እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ የሚደረግ ውጊያ አይደለም። እንደ አማኝ በምድር ላይ አሸናፊዎች ፣ ብርቱዎች፣ገዢዎች ፣አስፈሪዎች፣ ሆነን በክርስቶስ ተፈጥረናል። የተደረግነውን ማንነት በመጠቀም የዲያብሎስን ስራ ማፈራረስ የቤተክርስቲያን ድርሻ ነው። መንፈሳዊ ውጊያ የምናደርገው ሰይጣንን ለማሸነፍ ሳይሆን አሸናፊነታችንን ለማረጋገጥ ነው።

      ተጠናቀቀ !

      የእግዚአብሔር ድል ከእናንተ ጋር ይሁን !

      Kassu Boston

      Leave a comment