የእግዚአብሄርን ቤት ጓዳዎች እናፅዳ

በነህምያ ዘመን እንዲህ ሆነ፡፡ ነህምያ የኢየሩሳሌምን መፍረስና የበሮችዋን መቃጠል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ አለቀሰም፡፡ ከዚያም ከንጉሡ ፈቃድ አግኝቶ ኢየሩሳሌምን ሊሰራ በመጣ ጊዜ ሶስት ጠላቶች ተነሱበት፡፡ “ሐሮናዊውም ሰንበላጥ ባሪያውም አሞናዊው ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፡፡ ቀላል አድርገውንም ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድን ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወዳላችሁን? አሉን፡፡” ይላል (ነህ.2፥19) ከዚህም ሌላ በብዙ ማስፈራራትና ዛቻ፣ በደብዳቤም በሰውም ኢየሩሳሌም እንዳትሰራ የነህምያን ልብ ለመስበር ሞክረዋል፡፡ ነህምያ ግን የአምላኩ እጅ ከርሱ ጋር ነበረችና ሥራውን ጨረሰ

    ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ግን የኢየሩሳሌምን መሰራት ሲቃወም የነበረው ጦቢያ መኖሪያ ፍለጋ ወደ መቅደሱ አዘገመ። ኤልያሴብ ከሚባለው ካህን ጋር በመወዳጀትም በእግዚአብሔር ቤት ጓዳ ለመቀመጥ ቻለ፡፡ ነህምያ ስለዚህ ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል“ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሹሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ ለሌዋውያንና ለመዘምራን ….. እንደ ህጉ የተሰጣቸውን ለካህናቱም የሆነውን የማንሳት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን  ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር፡፡» (ነህ.13፥4-6) ይህ መንፈሳውያን ለሆኑ ሁሉ ታላቅ መልእክት አለው፡- የኢየሩሳሌምን መታነፅና መታደስ በፅኑ ሲቃወም የነበረው ተቃዋሚ ጠላት ጦቢያ ከእግዚአብሔር ቤት ውስጥ  ታላቁን ጓዳ ሲያገኝና በዚያ ሲቀመጥ ለነህምያና ዛሬም የነህምያ መንፈስ ለሆነላቸው እንዴት የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ ነው ! ያውም የተሰጠው ታላቁ ጓዳ እንደህጉ ለሌዋውያን ለመዘምራን ለበረኞች ለካህናት በአጠቃላይ ለመቅደሱና ለታላቁ ንጉሥ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች የተዘጋጀው መብል የሚቀመጥበት የከበረው ቦታ ነበር፡፡ መብል በሚቀመጥበት ቦታ  ውስጥ የእግዚአብሔር ህዝብ ጠላት ተቀምጦ ነበር፡፡ (ሚል.3፥10)

   ዛሬም በዚህ ቃል ራሳችሁንና መቅደሳችሁን ማለትም እግዚአብሄርን ማምለኪያና ህብረት ማድረጊያ ስፍራዎቻችሁን እንዲሁም መንፈሳዊ ጓዳችሁን ፈትሹ፡፡ ከካህኑ ወይም ከሐሰተኛ አገልጋዮች ጋር ተወዳጅቶ የእውነት ዓምድና መሰረት በሆነው በእግዚአብሔር ቤት ጓዳ ውስጥ የተቀመጠውን የዘመኑን ጦቢያ ሃሰተኛና አስመሳዩን ንቁበት፡፡ ይህም የዘረኝነት የግለኝነት (ቤተክርስቲያንን እንደግል ንብረት ማየት) የመጣላት የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት የሆነው አሮጌው ሰው ነው ፡  

     በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በተለይ አሁንም ጦቢያ “አሮጌው ሰው” ገዝፎ የሚታየው በታላቁ የአገልጋዮች የመዘምራን የሌዋውያን ጓዳ ነውና ነህምያዎች ሆይ ይህንን ጓዳ ለማፅዳትና ለእግዚአብሔር ለመቀደስ “ለመለየት” ትጉ፡፡ 

   ነህምያ ያደረገውን ተመልከቱ “ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦቢያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ፡፡ እጅግም አስከፋኝ፡፡ የጦቢያንም የቤቱን እቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጭ ጣልሁ፡፡ ጓዳዎቹንም እንዲያነፁ አዘዝሁ፡፡ የእግዚአብሔርንም ቤት እቃዎች፣ የእህሉንም ቁርባን፣ እጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ” (ነህ.13፥7-9) ይህ መልእክት ለኛም በዚህ ዘመን ላለን የወንጌል መልእክተኞች የተሰጠ የአደራ መልእክት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቤት ጓዳዎች እናፀዳ ዘንድ ይገባል፡፡ (ሮሜ.12፥1) ከጦቢያ፣ ከአሮጌው ሰው፣ ከስጋዊ ማንነት የፀዳ፣ የእውነት ዓምድና መሰረት የሆነውንም እውነተኛ የእግዚአብሔር መቅደስ ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ጦቢያ በተቀመጠበት ጓዳ የጠራና የሰባ የመንፈስ መብል የለምና፡፡ 

    መንፈሳዊ ቤት ሆኖ ለመሰራት ጓዳን ማጽዳት አስፈላጊ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል ፡፡ ጓዳን ማጽዳት ስል ያለ እግዚአብሄር ጸጋ የሚያገለግሉ የሚያስተምሩ የሚሰብኩ የሚዘምሩ እረኛ ነብያት ሃዋርያት የሆኑ እነዚህን ለይተን ማጽዳትና ጸጋው ያላቸውን መተካት ያስፈልጋል ባይ ነኝ ቤቱ አዲስ ሲሆን ልንረሳው የማይገባን ነገር ከአሮጌ ቤት አሮጌ እቃ ለቤቱ እንደማይመጥነው ለአዲሱ መንፈሳዊ ቤትም በአዲስ ቅባት የተቀቡ ለቤቱ የሚመጥኑ የመገልገያ እቃዎች ያስፈልጋሉና ይህንን ነህምያዎች ነቅተው እንዲለዩት ቤቱን እንዲያሳምሩት ያስፈልጋል

   ሌላው ደግሞ ዛሬ ጦቢያ ሆኖ በቤተክርስቲያን የተቀመጠ አላፈናፍን ያለና የእግዚአብሄርን መንፈስ ያዳፈነ የሰው ስርዐት ደንብና ህግ ይሆን ?? የእግዚአብሄር ህዝብ ሆይ ልንነቃ ይገባናል፡፡ ተባረኩልኝ፡፡

እባክዎን አንብበው ሲጨርሱ ላይክ የሚለውን ቢጫኑት ወደፊት የሚወጡ ጽሁፎችን በቀላሉ ማግኝት ይችላሉ በማንበብ ስለሚተባበሩኝም አመሰግንዎታለሁ

ካሱ ቦስተን

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ

Leave a comment