እናንተ የምድር ጨው ናችሁ !

እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። (ማቴዎስ 5፡13)

      የሰው ልጅ ጨውን ለብዙ መቶ ሺህ ዓመታት ለተለያየ አገልግሎት ሲተቀምበት ኖሯል አሁንም እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡  ጨው በዓለም ላይ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከ14,000 በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶች መዋሉን ሰለጨው ጥቅሞች በተለያዩ ድህረገጾች ላይ ተገልጾ ይገኛል፡፡ 

 ስለጨው ጥቅምና ጉዳት ለመዘርዘር ሳይሆን ለምንድነው ጌታ እኛን በጨው የመሰለን ? ለዚያውም የምድር ጨው ናችሁ ሲለን ምን ለማለት ፈልጎ ነው?  የሚለው ነጥብ ላይ ማተኮር ያስፈልገናል ስለዚህ በትንሹ ጨው ለምግብ ከሚሰጠው ጥቅም ጋር አያይዘን እንመልከተው ፡፡ 

ምግብ ለመበላት ሊጣፍጥ ይገባዋል፡፡ ምግብ የማይጣፍጠው ከሆነ ሰው ለመብላት አይበረታታም፡፡ ምግብን ለማጣፈጥ የሚጠቅመው ዋነኛው ነገር ደግሞ ጨው ነው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ሰብሰብ የማድረግ አቅም አለው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ወደ አንድ ደረጃ የማምጣት ችሎታ አለው፡፡  ጨው ምግቦችን ጣዕማቸው ሳይቀይር የማቆየት ብቃት አለው፡፡ ጨው የሚስብ ነገር አለው፡፡ ጨው በሁሉ ሰው ታዋቂና ተፈላጊ ጣእም አለው፡፡ ጨው በሁሉም አይነት ምግቦች ላይ ቀይ ወጥ: አልጫ ወጥ: ጎመን ወጥ: ሰላጣ: ፍርፍር: ወ.ዘ.ተ. ጨው የማይገባባቸው የምግብ አይነቶች የሉም፡፡ ምንም ያህል ድግስ ተደግሶ የሚያጣፍጥ ጨው ከሌለው ድግሱ ተመጋቢ ያላገኘ ድግስ ይሆንና የተዘጋጀው ምግብ ወደቆሻሻ መጣያ ስፍራ መወሰዱ አይቀሬ ነው ፡፡ ልክ ከእግዚአብሄር ጋር በክርስቶስ የመስቀል ስራ እንደታረቅን ወደ መንግስተ ሰማያት ያልገባነው በምድር ላይ ወሳኝ ስራ ስላለን ነው፡፡ ስለ   እኛ ስለተከታዮቹ ኢየሱስ ሲናገር የምድር ጨው ናችሁ ይላል፡፡

     ጨው የምግብን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው እኛ የምድርን የህይወት ደረጃ ከፍ እናደርገዋለን፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የመፍራት ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ካላሳየን ምድር እግዚአብሄርን ፈርቶ የሚያስፈራራው ምሳሌ አይኖረውም፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወት ምሳሌ ካልሆንን ምድር የእግዚአብሄርን መልክ ማየት አትችልም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ስለማክበር ሞዴል ካልሆንን አለም እግዚአብሄር እንዴት እንደሚከበር ምንም ፍንጭ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ በራስ የማይቻል ነገር በማድረግ እግዚአብሄር እንዳለ ካልመሰከርን ስለእግዚአብሄር መኖር የሚመሰክር ሰው አይኖርም፡፡ 

ጨው የምግብን የተለያየ ጣእም እንደሚሰበስበውና አንድ ወጥ ጣእም እንደሚሰጠው እኛም የምድርን ትኩረት ወደ ሰማይ የምናመለክተው እኛ ነን፡፡ እንዲሁም ከሞት በኋላ ህይወት አንዳለ አድርገን በመኖር ሌሎችንም የምናነቃውና ምድራዊ ህይወት ጊዜያዊ እንደሆነ አድርገን በመኖር ሌሎቹ ለዘላለማዊ ህይወት እንዲዘጋጁ የምናስጠነቅቀው እኛ ነን፡፡ በሰማይ ጌታ እንዳለው ሰው በመኖር ራስን በመግዛትና በዲሲፒን ኑሮ ክርስትና እንደሚቻል ፣ እግዚአብሄርን ማስደሰት እንደሚቻልና ለእግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ መኖር እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ የምንሆነው እኛው ነን፡፡

    ሰው በእግዚአብሄር አምሳል እንደተፈጠረና ለእግዚአብሄር ክብር እንደተሰራ በህይወታችን የምናመለክተው እኛ ነን፡፡  እግዚአብሄርን ማክበር የሰው በምድር ላይ የመፈጠር አላማ መሆኑን የምናስታውሰው እኛ ነን፡፡ ምድርን ከሚታይ ነገርና ከስጋዊ ፍላጎት ከፍ ያለን ደረጃ የምንሰጣት እኛ የምድር ጨው ነን፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ስለመኖር ለሌሎች የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሄርንና ሰውን በመውደድ እንዴት እንደሚኖር የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡

    ጨው ክብሩ ለምግብ ጣእም መስጠቱ ነው፡፡ የጨው ክብሩ ኮስታራነቱ ነው፡፡ እኛ ነን አለምን ማጣፈጥ የምንችለው፡፡ አለምን ለማጣፈጥ ጣእሙ ያለን እኛ ነን፡፡ እኛ ግን ይህንን ወሳኝ ሃላፊነታችንን ካልተወጣን ማንም ሊሰራልን አይችልም፡፡ እኛ አለምን ካላጣፈጥን እኛን ሊያጣፍጠን የሚችል አለም የለም፡፡ ጨው ደግሞ ካላጣፈጠ ለምንም አይጠቅምም፡፡

    ስለዚህ ነው ጨው በአለም ሁሉ መበተን ያለበት፡፡ ጨው በጨው እቃ ውስጥ ቢቀመጥ ምንም እንደማይጠቅም ሁሉ እኛም በየሰንበቱ መሰባሰባችንና ክርስትና ክርስትና ማለታችን ለሌላው ካልጠቀመ በጨለማው ላይ ካላበራና ለመራራው አለም ጣዕም ካልሰጠ ጠቃሚነቱ የማይታየው፡፡ ጨው ግን በተለያየ አይነት ወጥ ውስጥ ቢጨመር ያጣፍጣል ምግብ በሰሃን ተቀምጦ አጠገቡ በጠርሙስ ጨው መቀመጡ ምግቡን ሊያጣፍጠው እንደማይችል ነገር ግን  ከጠርሙሱ ውስጥ ወጥቶ ሊበተን እና ሊነሰሰነስ ይገባዋል ፡፡ ስለዚህ ክርስትያኖች የምንሰበሰበው ለመበረታታት ፣ ለመሞረድ ፣ ለመታደስ እና ለስራ ዝግጁ ሆነን ለመበተን እንጂ ስራው በምድር ፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ነው፡፡ ጨውነታችን በትምህርት ቤት ፣ በሆስፒታል ፣ በየፋብሪካውና በየኢንዱስትሪው በየስራ ስፍራችና በየሰፈራችን፣ በሃገር አስተዳደር ፣ በውትድር ፣ በንግድና በመሳሰሉት ሙያዎች ሁሉ ይፈለጋል፡፡

    እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 5፡13

    ክርስትናን ካለራስ ወዳድነት በፍቅር ለሌሎች መልካም ምሳሌ በመሆን ክርስትናን እንዲቀበሉ የምናበረታታው የምድር ጨው በመሆን ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ቤት ሆኖ መሰራት አንዱ ለዚህ መራራ ለሆነው አለም ጣዕም ለመስጠት ነውና  እንግዲህ እኛ የምንጠቀምበት ጨው ጨው ሆኖ ከማገልገሉ በፊት ብዙ ሂደቶችን አልፎ ነውና ለማጣፈጫነት የዋለው እኛም አለምን ለማጣፈጥ በእግዚአብሄር ቃልና በጸሎት እንዲሁም በሃይሉ ችሎት እየበረታንና እየተሰራን እንድንዘጋጅ መሰራታችንን እንቀጥል እላለሁ ተባረኩልኝ።

ካሱ ቦስተን 

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s