ጎልጎታ !    የመስቀሉ ስፍራ !

ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት መስቀሉንም ትሸክሞ በእብራይስጥ ጎልጎታ ወደተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ (ዮሃንስ 19:17)

    ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በመሃል አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ስፍራን ምክኒያት አድርጎ ለውዝግብና ለከፍተኛ የሰው መለያያ ወይም ሰዎችን በሃይማኖት ስም ጦርነት ማስከፈቻ ቅስቀሳ እየተሰራበት ያለ ትልቅ አጀንዳ ተይዞ ሊፈነዳ እያኮበኮበ ያለ ትልቅ የሃይማኖት ቦምብ የሚያከሽፈው የሃይማኖት አባት ካልተነሳ (ያውም ካለ ነው ምክኒያቱም አሁን የሃይማኖት አባቶች ከሚናገሩትና ከሚያስተምሩት ይልቅ ፖለቲካ ውስት ያሉ የአገር መሪዎች ሰውን የማረጋጋትና የማስታረቅ አገልግሎት እየታየ ስለሆነ) ይህ የሃይማኖት ቦምብ የፈነዳ እንደሆነ፤ ብዙ ሊያባራ የማይችል እልቂት እንደሚያስነሳ ከወዲሁ መገመት አያቅትም። ከአመታት በፊት የተፈጠረውን የቋንቋ እና የዘር መለያየትን ጥለን አንድ ወደመሆን እየመጣን ባለንበት ሰዓት በሃይማኖት ልዩነትን ማስነሳት ሊፈታ የማይችል ቁርሾ ሊያመጣ እንደሚችል ማወቅ አለብን። 

    በዚህ ዘመን ሰይጣን በሰዎች አይምሮ ውስጥ የራሱን ሃሳብ እየከተተ ሰውን ከሰው ጋር የሚያባላበትንና የሚያጨራርስበትን መንገድ በመቀየስ ላይ ነው። ወንድማማችነትን፤ ህብረትን፤ አንድነትን፤ መያያዝን፤ የማይፈልገው ሰይጣን አሁንም የአገራችንን ህዝብ ወደአንድነት መምጣት በመጥላት የተለያየ ሃሳብን እያመጣ ሲያነካክስና ሲያባላ ይታያል። ከአመታቶች በፊት ያለያየበትን የዘርና የቋንቋ  ልዩነትን ህዝቡ ነቅቶ በአንድነት ለመያያዝ ቋንቋና ዘር አይለየንም፤ በልዩነታችን አንድነታችንን አጠናክረን እንያያዝ፤ ባለበትና ለአንድነት በተነሳበት ሰዓት፤ይህንን ልዩነት ለማፍረስ እየሰራበት ያለውን ሃሳብ ልንነቃበት ያስፈልጋል።  

   ሰይጣን ሃሳቡን በሰዎች በተለይም በታዋቂ ሰዎች፤ ብዙ ህዝብ በሚከተላቸው ሰዎች ውስጥ እያስገባ ልዩነትን እየፈጠረ ሰዎችን ወንድማማቾችን፤ ቤተሰቦችን እንዲሁም ትዳርን ሁሉ ለማፍረስ እየጣረ ያለበት ጊዜ ነው። እባብ በተንኮሉ ሄዋንን እንዳሳታት ሃሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽህና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ፤ ብሎ ሃዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደጻፈላቸው፤ እኔም በዚህ ዘመን እባብ በተንኮሉ ሃሳባችንን ሊያበላሽና ሊያስተን ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነታችንና ንጹህነታችን እንድንለወጥና የሱን ሃሳብ እንድናከናውን ሊያደርገን እንዲሁም እርስ በርስ እየተነካከስን እንድንጠፋፋ ሊያደርገን ነውና ዛሬ እንንቃበት፤ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያምረውን አንድነታችንን እንጠብቅ፤ ህብረታችንን እናጠናክር። 

    የመስቀሉ ስፍራ ጎልጎታ ነውና በዚያ በጎልጎታ ከመስቀሉ ላይ የወጣው ድምጽ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የሚል ነው”፤ መስቀሉ ላይ ሰላም የተገኘበት፤ መስቀሉ ላይ ጥል ተገድሎ እርቅ የተገኘበት፤ መስቀሉ ላይ የአይሁድ ንጉስ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት፤ መስቀሉ ላይ ለሰው ልጆች ሃጢዓት ዋጋ ያውም የንጹህ የክርስቶስ ደም የተከፈለበት፤ መስቀሉ ለሚጠፉት ሞኝነት ሆኖ ለሚድኑት ግን የእግዚአብሄር ሃይል የሆነበት፤ መስቀሉ እግዚአብሄር ሰውን ከራሱ ጋር እንዲሁም ሰውን ከሰው ጋር ያስታረቀበት፤ መስቀል የሰው ትምክህት የተወገደበት፤ መስቀል ጨለማ ተገፎ ብርሃን የወጣበት፤ መስቀል በሰዎች ላይ የተጻፈውን እና ሰውን ወደፊት እንዳይራመድ በመንገዱ ላይ ብቅ እያለ አላስኬድ ያለውን የእዳ ጽህፈት ተደምስሶ ከመንገዱ የተወገደበት ነው። 

    መስቀል ሽክማችንን እና ቶሎም የሚከበንን ሃጢያትን ሁሉ የምናስወግድበት እንዲሁም የእምነታችንን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን እየተመለከትን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትእግስት የምንሮጥበት መንገዳችንም ነው። 

    ስለዚህ ወገኔ ዛሬ ልናስተውል የሚገባን የክርስቶስ መስቀል እኔና አንተ አንቺ የምንዋጋበት የምንጋደልበት ደማችንን የምናፈስበት ሳይሆን ሰላምና እርቅን ፈጥረን በአንድነትና በህብረት ዓይናችንን በመስቀሉ ላይ ወደተሰቀለው ክርስቶስ በማድረግ የመስቀሉን ስፍራ ጎልጎታን በምናባችን እያየን የምንጓዝበት ጊዜ እናድርገው። ሃዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈልን በሰይጣን እንዳንታለል የርሱን ሃሳብ አንስተውምና እንዳለን እናም የርሱን ሃሳብ እንንቃበት። 

    መስቀሉ የምንጣላበት የምንጋደልበት ሳይሆን በአንድነት በህብረት የመስቀሉ ሃይል ለሰው ልጆች ሁሉ እንደሆነ፡ በመስቀሉ ላይ የተሰራውን እየመሰከርን ሰውን ከእግዚአብሄር ጋር እና ሰውን ከሰው ጋር የምናስታርቅበት ይሁንልን፤ መስቀል ሰላማችን ነውና። አሜን! 

ካሱ ቦስተን 

እባክዎን ካነበቡ በኋላ ላይክ የሚለውን ይጫኑ እንዲሁም መልእክቱን ለሌሎች ያካፍሉ አመሰግናለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s